ባህር ዳር ከተማ አራት ተጫዋቾችን በይፋ አስፈርሟል

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩት ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠው ባህር ዳር ከተማ ሰሞኑን ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል በቃል ደረጃ የተስማማቸው አራት ተጫዋቾችን በዛሬው እለት በይፋ አስፈርሟል።

ወደ ሊጉ ገና በጊዜ ማደጉ የጠቀመው የሚመስለው ቡድኑ የአሰልጣኙን ውል ከማደስ ጀምሮ የተለያዩ ተጨዋቾችን ለማስፈረም እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ከአራቱ ተጨዋቾች መካከል የመጀመሪያው ከጅማ አባጅፋር ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳው እንዳለ ደባልቄ ነው። አሰልጣኙ ከሚከተለው የመስመር አጨዋወት አንፃር ይህ የመስመር አጥቂ ለቡድኑ አማራጭ ሊሆን የሚችለው እንዳለ ከጅማ አባጅፋር በፊት በደደቢት እና ሃዲያ ሆሳህና መጫወቱ ይታወሳል።

ቡድኑ ከእንዳለ በተጨማሪ አብርሃም ታምራትን ከኢትዮጵያ መድን ማምጣቱ ታውቋል። ቡድኑ በተከላካይ መስመሩ በኩል በአመቱ የተለያዩ ጥምረቶችን ሲያስመለክተን የቆየ ሲሆን የአብርሃም መምጣት በቦታው መረጋጋቶች እንዲኖሩት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው ቡድኑ የአማካይ መስመሩን ለማጠናከር ሁለት የአማካኝ መስማር ተጫዋቾችን አስፈርሟል። የመጀመሪያው በድሬዳዋ ከተማ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአርባ ምንጭ እና ወላይታ ድቻ የተጫወተው ታዲዎስ ወልዴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የውድድር ዓመቱን በሰበታ ከተማ ያሳለፈው ኤልያስ አህመድ ነው።

የጣናው ሞገዶቹ ከአራቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ ቶጎዋዊው የመሃል አጥቂ ጃኮ አራፋትን ለማስፈረም በቃል ደረጃ መስማማታቸው የታወቀ ሲሆን ተጨዋቹ በሃገር ውስጥ ባለመኖሩ አለማስፈረማቸውን እና ከሶስት ቀናት በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በይፋ እንደሚያስፈርሙት ተገልጿል።

የአሰልጣኝ ጳውሎስ ቡድን አሁንም ተጨማሪ ዝውውሮችን ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ሲገለፅ አዳዲስ ተጨዋቾችን ከማምጣት ጎን ለጎን ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ካደረጉት እና በዓመቱ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩ 9 ተጨዋቾችን ከክለቡ ጋር በቀጣይ ለማቆየት ውላቸውን እያደሰ ይገኛል።