ፋሲል ዘጠነኛ ተጨዋቹን አስፈርሟል

ፋሲል ከነማ በ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠናክሮ ለመቅረብ ከአሰልጣኝ ቅጥር ጀምሮ በርካታ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ እየቀላቀለ ሲሆን ዛሬ ከሰዓት ዘጠነኛ ተጨዋቹን ማስፈረሙን በይፋዊ ገፁ አስታውቋል።

ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ወደ ቡድኑ ካመጣ በኃላ በርካታ ተጨዋቾችን ከፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ሲያስፈርም ቆይቶ በዛሬው እለት ፋሲል አስማማውን በሁለት አመት ኮንትራት ከፍተኛ ሊግ ላይ ከሚወዳደረው ከለገጣፎ ከተማ አስፈርሟል።

ፋሲል በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት ለለገጣፎ ከተማ 9 ጎሎችን በማስቆጠር አጠናቋል። አሰልጣኝ ውበቱ እስካሁን የአጥቂ መስመር ተጨዋች አለማስፈረማቸው አግራሞት የፈጠረ ቢመስልም ፋሲልን ማምጣታቸው የአጥቂ መስመር ክፍሉን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።

ቡድኑ ከዚህ በፊት የ7 ነባር ተጨዋቾችን ውል ማደሱ እና 8 ተጨዋቾችን ማስፈረሙ ይታወሳል።