ኢትዮጵያ ቡና እና ዕልባት ‘ቲፎዞ’ የተሰኘውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዛሬ አስተዋወቁ

ዕልባት ማኔጅመንት ቴክኖሎጂ ሶሉሽን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ‘ቲፎዞ’ የተሰኘ የተቀናጀ ዲጂታል የስፖርት ፕላትፎርም በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበት ጋር በመተባበር ተግባራዊ ማድረግን በሚመለከት ዛሬ ከሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ።

በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ማህበር እያደረጉ ለሚገኙት ዘርፈ ብዙ ክለቡን የማሳደግ ስራዎች እና እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ የተባለለትን እና በዕልባት ሶሉሽን በኩል የቀረበት ‘ቲፎዞ’ ስለተሰኘ የተቀናጀ ዲጂታል የስፖርት ፕላትፎርም ትግበራ አስመልክቶ ማብራሪያዎች ተሰጥቷል። መግለጫውን ለመስጠት የክለቡ የቦርድ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ የዕልባት ማኔጅመንት ዋና ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ራያ እና የኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ክፍሌ አማረ የተገኙ ሲሆን በክብር እንግድነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራን ጨምሮ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው ግለሰቦች ተገኝተዋል።

ፕሮግራሙን በንግግር የጀመሩት የዕልባት ማኔጅመንት ዋና ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ራያ ስለ ቴክኖሎጂው እና ስለ ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል። “በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ይህንን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከእኛ ጋር ለመስራት ፍቃደኛ በመሆናችሁ በጣም እናመሰግናለን። ይህንን ዘመናዊ አሰራር ያመጣንበት ዋና አላማ ክለቦች ከደጋፊዎቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ቀላል መንገድ ለመፍጠር ነው። በውጪ ዓለማት እንደምንመለከተው ክለቦች የሚያቀርቡትን መለያዎችን እና የተለያዩ ቁሳቁሶች በተደራጀ እና በተመቸ አሰራር ነው ለደጋፊዎቻቸው የሚሸጡት። ነገር ግን እኛ ሃገር ይህ ሁኔታ የለም ስለዚህ ይህንን ቀልጣፋ አሰራር ወደ ሃገራቸን ማምጣት እንዳለብን በማመን ነው ስራዎችን ለመስራት የተንቀሳቀስነው” ብለዋል።

አቶ ነፃነት ጨምረውም ክለቦች የሚያቀርቡትን ሸቀጣ ሸቀጦች ብቻ ሳይሆን ደጋፊዎቻቸውንም በህጋዊ መንገድ በዚህ አሰራር መመዝገብ እንደሚችሉበትን መንገድ ቴክኖሎጂው እንደሚሰራ አስረድተዋል። “በዚህ ቴክኖሎጂ ክለቡ ደጋፊዎቹን በቀላሉ በህጋዊ መንገድ መመዝገብ ይችላል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና የተመዘገቡ ከ18ሺ በላይ ደጋፊዎች እንዳሉት እናውቃለን። ነገር ግን ከዚህም በላይ ቁጥር መብዛት ይችላል፤ ይህንን ደግሞ ለማድረግ በቀላሉ ደጋፊዎች ሳይጉላሉ ያሉበት ቦታ ሆነው ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሊመዘገቡ ይችላሉ” ብለዋል።

ማብራሪያቸውን የቀጠሉት አቶ ነፃነት ቴክኖሎጂው ከፊታችን ሰኞ ነሃሴ 28 ቀን ጀምሮ በየአካባቢው በሚገኙ በተመረጡ የዕልባት ወኪሎች የሙከራ ስራ የሚጀምር መሆኑን ተናግረው በተለይ በቀጣይ በሚደረገው ዓመታዊ የቤተሰብ ሩጫ ላይ ከሚገኙ 25ሺ በላይ ተሳታፊዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን በዲጂታል ስርዓት ለማካተት እንደታቀደ አስረድተዋል። ከዚህም ተከታታይ የሙከራ ስርዓቶች በኃላ በመጪው አዲስ አመት በመላው ሀገሪቱ እና የክለቡ ደጋፊዎች በብዛት ይገኙባቸዋል ተብለው በጥናት ከተለዩ ሀገራት መካከል በአሜሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በተመረጡ የአውሮፓ ከተሞች ስራው ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።

በመቀጠል የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የቦርድ ፕሬዝዳንት የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ስለ ስምምነቱ እና ስለ ቴክኖሎጂው ማብራሪያ ሰተዋል። “ከእልባት ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ጋራ ለረጅም ጊዜ ውይይት አድርገናል። ምክንያቱም ፕሮጀክቱ ትልቅ ስለሆነ በደምብ ማጤን እንዳለብን አውቀን ጥያቄዎችን ስንጠይቅ ነበረ።’ይኼ ፕሮጀክት የእውነት ተግባራዊ መሆን ይችላል?’ የሚለው የመጀመሪያ ጥያቄያችን ነበር። ሁለተኛው ጥያቄያችን ደግሞ ‘ፕሮጀክቱ ባይስማማን እንዴት አድርገን ነው መውጣት የምንችለው?’ የሚለው ነበር። እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ በቦርዱ በኩል ስለ ቴክኖሎጂው ምንነት በጉዳዩ ላይ በቂ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ምክር እንዲሰጡን ከመጠየቅ በተጨማሪ አንድ የህግ ባለሞያም በውሉ ጉዳይ እንዲያማክሩን አድርገናል።” ብለዋል።

መቶ አለቃ ፈቃደ አክለውም  “በዚህ ቲፎዞ በሚል በተሰየመው ፕሮጀክት ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ደጋፊው ነው። ከደጋፊው ሚና በኋላ ደግሞ አስፈላጊውን ለገበያ የሚቀርቡ ቁሳቁሶችን በማዘጋጀት ለደጋፊው ማድረስ ያለበት ክለቡ ነው። እስከዛሬ ድረስ ልዩ ልዩ ነገሮችን እንሸጥ የነበረው አዲስ አበባ እና አካባቢው ላይ ላሉ ደጋፊዎቻችን ብቻ ነው። አሁን ግን በዚህ አሠራር በመላው ኢትዮጵያ፤ ከዚያም አልፎ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና አሜሪካ ለሚገኙ ደጋፊዎቻችን የምንሸጠውንም ዕቃ ሆነ የምንሰራውን ስራ ለማስተዋወቅ እንችላለን።” በማለት ስለቴክኖሎጂው ጥቅም አስረድተዋል።

“በሜዳችን በምናደርገው ጨዋታ ከቲኬት ሽያጭ መጠቀም መብታችን ቢሆንም ይህን የምንጠቀመው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚሰጠንን ሜዳ ታሳቢ አድርገን ችግሮችን ከፈታን በኃላ ነው። በዚያ ጉዳይ ላይ የፌዴሬሽኑን ትብብር እንጠይቃለን። ቲኬታችንን ራሳችን ሸጠን ገቢያችንን ወደራሳችን ለማድረግ ስንችል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሜዳዎች ላይ የምንጫወት ከሆነም ከቲኬቱ ገቢ የሚገባቸውን ድርሻ ደግሞ እንከፍላለን። በዘመናዊ መልክ ደጋፊዎቻችንን ለማስተናገድ ከዚህ የተሻለ አማራጭ የለም። በዚህ አሠራርም ገቢው የቡና እስከሆነ ድረስ በውጪ ሃገርም ሆነ በሃገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ደጋፊዎቻችን ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን  ቲኬቱን በመግዛት ክለባቸውን መደገፍ ባይመለከቱምይችላሉ።” በማለት አጠቃለዋል።

ከመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በመቀጠል ማብራሪያ የሰጠው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ክፍሌ አማረ ስለ ደጋፊዎችን የመመዝገብ እና ህጋዊ ስለማድረግ ምላሽ ሰጥቷል። “በአሁኑ ሰዓት በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡት የደጋፊዎች ቁጥር 18 ሺ ነው። ነገር ግን ሰሞኑን ባስጠናነው ጥናት መሰረት ክለቡ ከ6 ሚሊዮን በላይ ደጋፊዎች እንዳሉት አረጋግጠናል። ስለዚህ ቢያንስ 100 ሺው እንኳን ህጋዊ ሆኖ ወርሃዊ መዋጮ ቢያደርግ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ክለቡ ያገኛል። ይህንን ደግሞ ለማድረግ ከዕልባት ጋር ያደረግነው ስምምነት ነገሮችንን ያቀሉልናል ብለን እናምናለን።” ብለዋል።

በመግለጫው ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በ40 ማዕከላት ቴክኖሎጂው ስራውን እንደሚጀምር የተገለፀ ሲሆን ወደ ፊት ወደ እያንዳንዱ ደጋፊ ለመቅረብ ስራዎች እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።

በመቀጠልም ቴክኖሎጂውን የማስተዋወቅ ፕሮግራም የተከናወነ ሲሆን ከቴክኖሎጂው ጎን ለጎን ዘመናዊ የደጋፊዎች የአባልነት ካርድ ለታዳሚያኑ ተዋውቋል። የቡና ካርድ ተብሎ ስያሜ ያገኘው ህጋዊ የደጋፊዎች ካርዱ ለአያያዝ አመቺ መሆኑን እና ደጋፊው ቢጠፋበት በጀርባው ባር ኮዶች ስላሉት ሌላ ሰው እንደማይገለገልበት ተገልጿል። ዲጂታል የሆነው ይህ ካርድ አገልግሎት ላይ ሲውል ከፕላቲንየን ጀምሮ እስከ የተማሪዎችን አቅም እስካማከለ የክፍያ ፓኬጅ እንዳለ ተጠቁሟል።

በስተመጨረሻ ከታዳሚያኑ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ላይ ዳግም ማብራሪያ ተሰቶባቸዋል። ፕሮግራሙ ከመጠናቀቁ በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ስለ ቴክኖሎጂው ጥሩነት ተናግረዋል። “ቴክኖሎጂው በጣም ጥሩ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ቡናን ብቻ ሳይሆን ሃገራችንንም ነው የሚጠቅመው። እንደዚህ አይነት ዘመናዊ አሰራሮችን ሌሎች ክለቦችም ሊኮርጁት ይገባል” ብለው የቴክኖሎጂው ተግባራዊነት ላይ ተግቶ መስራት እንዳለበት በመጠቆም አጠቃለዋል።

ከመግለጫው በኃላ ለታዳሚያኑ የእራት ግብዣ የተደረገ ሲሆን ስለ ቴክኖሎጂው አጠቃቀም ማብራሪያዎችም ተሰጥተዋል።