ሳሙኤል ሳኑሚ በጃፓን የመጀመሪያ ጨዋታው ግብ አስቆጥሯል

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን ለቅቆ በጃፓን 4ኛ ዲቪዝዮን ለሚጫወተው ቴጌቫያሮ ሚያዛኪ የፈረመው ናይጄሪያዊው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ ለአዲሱ ክለቡ ባደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ ግብ ለማስቆጠር ችሏል።

ሳኑሚ ክለቡ በሊጉ ሁለተኛ ዙር አምስተኛ ጨዋታ ቪርታየን ኩዋናን ገጥሞ 3-2 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ የመጀመሪያውን ግብ ከመረብ አሳርፏል። የ26 ዓመቱ አጥቂ ግብ ከማስቆጠሩም በተጨማሪ ለሁለተኛው ግብ መቆጠር ምክንያት የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን የጨዋታው ኮከብ ሆኖ እንደተመረጠም ታውቋል።

የተጫዋቹ ወኪል ቶፔ አላቢ ዶዶ ለስኮር ናይጄሪያ ድረገፅ በሰጡት መረጃ “ሳኑሚ ክለቡ ከሜዳው ውጪ ከኋላ ተነስቶ ማሸነፍ በቻለበት ጨዋታ አንድ ግብ ሲያስቆጥር ለሌላ ግብ ደግሞ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ጨዋታው ለአዲሱ ክለቡ ያደረገው የመጀመሪያው የነጥብ ጨዋታ ነበር። በጃፓን ባደረገው አጀማመር ደስተኛ ነው፤ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር እና ድሎችን ለማስመዝገብ ተዘጋጅቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

የእግርኳስ ህይወቱን በሌጎሱ ዩንየን ባንክ ክለብ የጀመረው ሳኑሚ በ2003 ዓ.ም. በዩጎስላቪያዊው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የወቅቱ አሰልጣኝ ዮርዳን ስቶይኮቭ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ እስካለፈው የውድድር ዓመት ድረስ በሃገራችን ቆይታ አድርጓል። አጥቂው ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና መጫወት የቻለ ሲሆን በ2006 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በ2007 ዓ.ም. የደደቢት ቆይታው ደግሞ በ22 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ መጨረስ ችሏል።