ሀዋሳ ስታድየም እድሳት ተደርጎለታል

የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ሀዋሳ ከነማ እና የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ደቡብ ፖሊስ በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚያከናውኑበት የሀዋሳ ስታድየም እድሳት ተደርጎለታል፡፡ ስታድየሙ የሰው ሰራሽ ሣር የተነጠፈለት ሲሆን የትሪቡን እድሳት እና የመም (ትራክ) ማሻሻያ ተደርጎለታል፡፡

የሰው ሰራሽ ሣሩ በአቶ ሳህሉ ገብረወልድ አመራር ወቅት ከፊፋ የተለገሰ ሲሆን በ2 ሆላንዳውያን መሃንዲሶች የተከላ ስራው ተከናውኗል፡፡ ሜዳው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሲሆን የሜዳው ወርድ እና ቁመት በመጠኑ ማሻሻያ ተደርጎለት እንዲጠብ ተደርጓል ተብሏል፡፡

ለስታድየሙ እድሳት እስከ 17 ሚልዮን ብር ወጪ መደረጉ ሲታወቅ ከፍተኛውን ገንዘብ የፈጀው የትሪቡን እድሳት ስራው ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ለተመልካች እና ለሚጫወቱ ቡድኖች አስቸጋሪ አዋራ የነበረው የመሮጫ መም (ትራክ) መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎለት ቀይ አሸዋ ተነጥፎበታል፡፡

በአዲሱ የሰው ሰራሽ ሣር ሀዋሳ ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ሁለት ጊዜ የዝግጅት ጨዋታ ባለፉት ሳምንታት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን የስታድየሙን እድሳት በማስመልከት የከተማ መስተዳድሩ በዚህ ወር መጨረሻ 5 የደቡብ እና 3 የአዲስ አበባ ክለቦችን ያካተተ ውድድር ለማካሄድ ማሰቡ ታውቋል፡፡ ውድድሩ ስታድየሙን ለመመረቅ ከማሰብ በተጨማሪ ገቢ ለማግኘት መታሰቡም ተነግሯል፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ ለመጫወት አመቺ ካልሆኑ ሜዳዎች አንዱ የነበረው የሀዋሳ ስታድየም ከአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታድየም በመቀጠል በኢትዮጵያ 2ኛው ባለ ሰው ሰራሽ ሣር ሆኗል፡፡ የስታድየሙ መታደስም ለሃዋሳ ከተማ የስታድየም አማራጭ ይፈጥራል ተብሎለታል፡፡

በከተማው 40ሺህ ተመልከቾችን ማስተናገድ የሚችለው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ስታድየም ግንባታ 70 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህ አመት የሚካሄደው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል፡፡ ይህ ስታድየም በክረምቱ የብሄራዊ ቡድኑን ዝግጅት ማስተናገዱ የሚታወስ ነው፡፡

outside stadium4

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው ስታድየምም የጥራት ደረጃው ላቅ ያለ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡ ስታድየሙ ተመልካች የመያዝ አቅሙ ዝቅተኛ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ብቸኛው ሙሉ ለሙሉ ወንበር የተገጠመለት ስታድየም ነው፡፡

11252015_928610397199647_606673668981447827_o

ፎቶ ከላይ – ሰው ሰራሽ ሜዳ የተነጠፈለት ሀዋሳ ስታድየም – ፎቶ ፌስቡክ ገፅ

መካከል – በመጠናቀቅ ላይ ያለው አዲሱ ባለ 40ሺህ መቀመጫ ስታድየም ውጫዊ ገፅታ

ከታች – የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በዋናው ግቢ ያስገነባው ስታድየም ከፊል ገፅታ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *