የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከቡርኪና ፋሶ ጋር በኦጋዱጉ በቀጣይ ቅዳሜ የሚያደርገው የጠአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ማጣርያ ጨዋታ በሃገሪቱ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት በቡርኪና ፋሶ የመካሄዱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
ለ27 አመት ስልጣን ላይ ቆይተው ባለፈው አመት ከስልጣን የተወገዱት ብሌስ ኮምፓሬ ታማኝ እንደሆነ የሚነገርለት በጄኔራል ጂልበርት ዴንዴሬ የሚመራ የቡርኪናፋሶ የጦር ኃይል ባለፈው ሐሙስ በሽግግር መንግስቱ ላይ መፈንቅለ መንግስት ማካሄዱንና ሃገሪቱን መቆጣጠሩን በብሄራዊ ቴሌቪዥን ማወጁን ተከትሎ በሃገሪቱ አለመረጋጋት ሰፍኗል፡፡ ከ3 ሳምንት በኋላ ሃገራዊ ምርጫ ልታደርግ አቅዳ የነበረችው ሃገርም በትርምስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ በጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ ነውጥም እያስተናገደች ትገኛለች፡፡
ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት ለካፍ ጥያቄ እንዳቀረበ የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት አቶ ወንድምኩን አላዩ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ስለ መፈንቅለ መንግስቱ መረጃው ደርሶናል፡፡ ወደ ቡርኪናፋሶ የሚደረጉ በረራዎችም ተቋርጠዋል፡፡ ወደፊት መሆን ስለሚገባው ነገር ለካፍ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ውሳኔውንም እየጠበቅን ነው›› ብለዋል፡፡
የካፍ ምላሽ በፍጥነት የሚታወቅ ከሆነ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከቡርኪና ፋሶ አቻው ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በጎረቤት ሃገራት ሊካሄድ ይችላል፡፡
ከ12 አመታት በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለቱኒዚያ የ2004 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወርቃማ እድል የነበረው ቢሆንም በመፈንቅለ መንግስት ትርምስ ስትታመስ ከነበረችው ላይቤርያ ጋር በሞኖሮቪያ ተጫውታ 1-0 ተሸንፋለች፡፡ በአንፃሩ የጊኒ ብሄራዊ ቡድን ከላይቤርያ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ በጎረቤት ሃገር ጋና እንዲደረግ ለካፍ ጥያቄ በማቅረብ በገለልተኛ ሜዳ አሸንፋ ማለፏ የሚታወስ ነው፡፡