ካስቴል ቢራ የፕሪሚየር ሊጉን የስያሜ መብት ገዛ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የካስቴል ቢራ ጠማቂ ከሆነው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር የፕሪሚየር ሊጉ ስያሜ መብት የመሸጥ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለቀጣዮቹ 2 የውድድር ዘመናት ካስቴል ቢራ የሚጠራ ሲሆን ለስያሜው ፌዴሬሽኑ በሁለት አመታት ውስጥ 14 ሚልዮን ብር ያገኛል፡፡

በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተደረገውን የፊርማ ስነ ስርአት የቢጂአይ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ሃደራ እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ አከናውነዋል፡፡

የስምምነት ፊርማው ከተፈረመ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በሰጡት ማብራርያ ስምምነቱ የገንዘብ አቅማቸውን እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡

‹‹ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የእግርኳስ እቅስቃሴ ለማሳደግ ፣ ተወዳዳሪነቱን እንዲጨምርና በውጤት እዲደገፍ ለማድረግ በፋይናንስ አቅሙ መዳበር እንዳለበት እናምናለን፡፡ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር የተፈራረምነው ውልም የዚህ አካል ነው፡፡ ለዘመናት የእግርኳሳችን ችግር ሆኖ የቆየው የፋይናንስ ችግርን ለቅረፍ በማሰብ ነው ይህንን ስምምነት የተፈራረምነው፡፡ የስፖንሰርሺፑ ዋና አላማ ፕሪሚየር ሊጉ ከፕሮግራም አወጣጥ ጀምሮ ለአሸናፊዎች እስከሚሰጠው ሽልማት ድረስ ያለውን ወጪ ለመሸፈን የሚሆን ገቢ ማግኘት ነው፡፡

‹‹ በስምምነቱ ዙርያ ሊጠየቁ የሚችሉ ጥልቅ የአሰራር እና የገንዘብ ጥያቄዎች ሊመጡ ቢችሉም እንዲህ አይነት ስምምነቶች ለእግርኳሳችን ያልተለመዱ በመሆናቸው ቀስ በቀስ እየዳበረ የሚመጣ ነው፡፡ ዋናው ነገር መጀመራችን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በሂደት እያስተካክንና ክፍተቶችን እየደፈንን እንሄዳለን፡፡ ››

IMG_1912

የቢጂአይ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ሃደራ በበኩላቸው የሊጉ ብራንድ ማደግ ለሃገሪቱ እግርኳስ ማደግ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ ኢንቨስትመንት ወደ ሃገራችን ሲገባ ትልቁ ጥቅሙ ሰራኞችን መቅጠር እና ለመንግስት ገቢ ማስገባት ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይም መሳተፍ ነው፡፡ ባደጉት ሃገራት እንደሚደረገው ትልልቅ ኩባንያዎች የሃገራቸውን ሊጎች ስፖንሰር ያደርጋሉ፡፡ እኛም ፕሪሚየር ሊጉን እንደ አንድ ብራንድ በማስተዋወቅ ህፃናት ልጆች እንደሌሎች ሙያዎች እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን እንዲነሳሱ እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲተዋወቅ እንፈልጋለን፡፡ ለአንድ ሃገር እግርኳስ እድገት ከመሰረተ ህዝብ ስራዎች በተጨማሪ ፕሪሚየር ሊጉን ወደ ብራንድ ደረጃ ማሳደግ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህ አላማ ነው ስምምነቱን የተፈራረምነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሪሚየር ሊጉን ስያሜ ሲሸጥ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ በ2000 የውድድር ዘመን የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ለአንድ አመት በ1.5 ሚልዮን ብር ሊጉን ስፖንሰር አድርጎት ነበር፡፡ በወቅቱ ስያሜው ሚድሮክ ሚሌንየም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚል ነበር፡፡ በ2005 ደግሞ በስፖንሰር ሺፕ መልኩ ባይሆንም በነሃሴ 2004 ህይወታቸው ባለፈው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ስም የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ መለስ ዋንጫ ተብሎ ተሰይሞ ነበር፡፡

ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም የሚጀመረው ካስቴል ፕሪሚየር ሊግ ከሌላው ጊዜ የተሸለ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፌዴሬሽኑ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥራዊ መረጃ ከሚያቀርበው R&D GROUP ጋር የሊጉን ጨዋታዎች በቁጥራዊ መረጃ ለመተንተን ስምምነት ላይ መድረሱ የሚታወስ ሲሆን የተመረጡ የአዲስ አበባ እና የክልል ጨዋታዎችን በቴሌቪዥን ለማስተላለፍም ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ከስምምነት ደርሷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *