ሪፖርት | ሲዳማ ቡና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዛሬ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና ወደ ሊጉ ካደገበት 2002 ጀምሮ አሸንፎት የማያውቀውን ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ጨዋታው የስራ ቀን ላይ የተካሄደ እንደመሆኑ ከደጋፊዎች አንፃር መጠኑ ያነሰ እንደሚሆን ቢገመትም ቀስ በቀስ በርካታ የሲዳማ ቡና እንዲሁም ከአዲስ አበባ ድረስ ተጉዘው በመጡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተጨምረው ለስታዲየሙ ውበት ሆነዋል። ባለ ሜዳው ሲዳማ ቡና አዳማ ላይ ከተጠቀመው አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጎ ፍቅሩ ወዴሳ፣ አበባየሁ ዮሀንስ፣ ዳዊት ተፈራ፣ መሐመድ ናስር እና በቅጣት ያልነበረው ሐብታሙ ገዛኸኝን በመሣይ አያኖ፣ ዮሴፍ ዮሀንስ፣ ወንድሜነህ ዓይናለም፣ ፀጋዬ ባልቻ እና ጫላ ተሺታ ሲተካ በፈረሰኞቹ በኩል በሜዳቸው ስሑል ሽረን ከረቱበት አሰላለፍ አሌክስ ኦሮትማልን በአቤል ያለው ብቻ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ፌድራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በልዩ የዳኝነት ብቃት በመሩት ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች የፈረሰኞቹ የበላይነት የታየበት ቢመስልም ቀስ በቀስ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ጨዋታ በመግባት ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ተመልክተናል። በ2ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጭ ተብላ በተሻረችው አጋጣሚ ነበር የግብ ሙከራን ገና በጊዜ መመልከት የቻልነው። 7ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም መስፍን ከግቡ ትይዩ ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ ቢመታትም መሣይ አያኖ ያወጣበት ሙከራ ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የመጀመርያው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

ከሦስት ደቂቃዎች በኃላ ግርማ በቀለ ከርቀት አክርሮ መትቶ የግቡ አግዳሚን ታኮ ሲወጣበት በዛሬው እለት ተዳክሞ የታየው የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ መስመር ሲፈትኑ የነበሩት ሲዳማ ቡናቸዎች በ35ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ግባቸውን አስቆጥረዋል። ጫላ ተሺታ በመስመር በኩል ኄኖክ አዱኛን አልፎ ወደ ግብ ክልል ያሻገራትን ኳስ ልማደኛው አዲስ ግደይ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሯት ቡናማወቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በዚህች ግብ መነቃቃታቸው በጉልህ ሲታይ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በአዲስ ግደይ ተደጋጋሚ መከራን ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ሲቀር ፈረሰኞቹም አቻ ለመሆን ያደረጉት ጥረት በግብ አጋጣሚዎች ሳይታጀብ የመጀመርያው አጋማሽ በሲዳማ ቡና 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴን ሲያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች በጎል ሙከራዎች በኩል የተሻሉ ነበሩ። 48ኛው ደቂቃ ላይም አጥቂው ፀጋዬ ባልቻ በግራ በኩል ኄኖክ አዱኛን በአስደናቂ መልኩ ካለፈ በኃላ ያቀበለውን ኳስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የገባው የቀድሞው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን አጥቂ ጫላ ተሺታ ወደ ግብ ክልል እየገፋ ገብቶ በመምታት በኬንያዊው ግብ ጠባቂ ፓትሲክ ማታሲ መረብ ላይ አሳርፎ የሲዳማ ቡና የግብ ልዩነት ወደ ሁለት ማሳደግ ችሏል።

ፈረሰኞቹ የሁለቱን ግብ ልዩነት በማጥበብ ከጨዋታው ነጥብ ለማግኘት በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል። 55ኛ ደቂቃ ከማዕዘን ምት አብዱልከሪም ሲያሻማ ሙሉዓለም መስፍን በግንባር ገጭቶ በግቡ ቋሚ ብረት ስር ታካ ስትወጣበት አሜ መሐመድ ከአብዱልከሪም የተመቻቸለትን ኳስ ያመከነበት ሙከራዎችም ተጠቃሾች ነበሩ። 65ኛው ደቂቃ ሙሉዓለም መስፍን ከመሐል የሜዳው ክፍል ወደ ግብ የላካት ኳስ የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ዮናታን ፍሰሀንና ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ አቤል ያለው በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር የፈረሰኞቹን ተስፋ ማለምለም ችሏል።

71ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ገብቶ መልካም እንቅስቃሴን ያደረገው ዳዊት ተፈራ ለፀጋዬ ባልቻ ሰቶት ፀጋዬ አገባው ሲባል ግልፅ አጋጣሚን አግኝቶ በአስቻለው ታመነ ድንቅ ብቃት የተነጠቀበት ኳስ ለሲዳማ ተጨማሪ ግብ ሊሆን የሚችል አጋጣሚ ሲሆን ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል አቤል ያለው ፈቱዲን ጀማል የፈጸመውን ስህተት ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ያገኛት አስቆጪ እድል በመሣይ አያኖ ከሽፎበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳያስተናግድ ሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሲዳማ ቡና በ2002 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገ በኋላ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጋቸው 18 የሊግ ጨዋታዎች አሸንፎ የማያውቅ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ በታሪኩ የመጀመርያውን ድል ማስመዝገብ ችሏል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ: LINK