ቻምፒዮንስ ሊግ | አህመድ ሽሀብ ስለ አል አህሊ እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ ይናገራል

“አል አህሊ ለጅማ አባ ጅፋር ተገቢውን ክብር ይሰጣል” ጋዜጠኛ አህመድ ሽሀብ 

የግብፁ ታላቅ ክለብ አል አህሊ እና የኢትዮጵያው ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋርን የሚያገናኘው የቻምፒዮንስ ሊግ አንደኛ ዙር ጨዋታ ነገ ምሽት 02፡00 በአሌክሳንድሪያ ይደረጋል።  

ባሳለፍነው ወር በ2018ቱ የአህጉሪቱ ትልቁ ውድድር ፍፃሜ በቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ የተረታው አል አህሊ የአምናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋርን በማስተናገድ ነው የዘንድሮ ውድድሩን የሚጀምረው። ይህን ጨዋታ የተመለከቱ በአል አህሊ ዙሪያ ያሉ ነጥቦችን አስመልክቶም በግብፁ ጋዜጣ አክባር ኤልዮም ላይ የሚፅፈው ጋዜጠኛ አህመድ ሽሀብ አስተያየቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥቷል።

በአፍሪካ መድረክ ስማቸው የገነነው እና ቻምፒዮንስ ሊጉን ለስምንት ያህል ጊዜ በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት አል አህሊዎች በኤስፔራንስ 3-0 የተሸነፉበት ሁለተኛው የፍፃሜ ጨዋታ ከሠላሳ ሦስት ቀናት በፊት የተደረገ ነበር። ይህ መሆኑ ክለቡ ከቻምፒዮንስ ሊጉ መንፈስ ሳይርቅ ዳግም የዘንድሮውን ውድድር እንዲጀምር የሚረዳው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ጨዋታው በሽንፈት የተደመደመ እንደመሆኑ መጠን የሚያሳድረው ተፅዕኖ ሊኖር ይችላል። ይህን አስመልክቶ አህመድ በክለቡ ዙሪያ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ በዚህ መልኩ አስረድቷህ። ” አል አህሊ ዋንጫውን ካጣ በኋላ ከአረብ ሊግም በጊዜ በመሰናበቱ አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። የተመዘገቡት ውጤቶችም ለፈረንሳዊው አሰልጣኝ ፓትሪክ ካርትሮ ስንብት ምክንያት ሆነዋል። ነገር ግን የቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ መሐመድ ዩሱፍ በግብፅ ሊግ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ድል ማድረግ ችለዋል። በመሆኑም የነገውንም ጨዋታ በተመሳሳይ ሁኔታ በማሸነፍ ጥሩ ጅማሮ ለማድረግ ያስባሉ” ይላል።

ምንም እንኳን ስለ ግብፁ ክለብ ታላቅነት ብዙ ማለት ቢቻልም አምና ወላይታ ድቻ በሌላው የግብፅ ኃያል ዛማሌክ ላይ ያስመዘገበው ድል ለኢትዮጵያው ክለብ ጅማ አባ ጅፋር መነሳሳትን ሊፈጥርለት እንደሚችል ይታመናል። የአህመድ ሀሳብ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ” አምና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ዛማሌክ በኢትዮጵያ ክለብ ተሸንፏል። ሆኖም የዛማሌክ ሽንፈት የተከሰተው የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢዎች በተጫዋቾች ምርጫ እና በተለያዩ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ እጃቸውን በማስገባታቸው ነው። አል አህሊ ግን ለተጋጣሚው ጅማ አባ ጅፋር ተገቢውን ክብር በመስጠት እና ጨዋታውን በማሸነፍ ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት ዝግጁ ሆኗል።” በማለት ምክንያቱን ያስቀምጣል።

በመጨረሻም አህመድ ሽሀብ ነገ በሚደረገው ጨዋታ ላይ ለአል አህሊ ልዩነት ይፈጥራሉ ያላቸውን ሁለት ተጫዋቾች ጠቁሟል። እንደ ጋዜጠኛው ሀሳብ ከ2011 ጀምሮ በክለቡ ውስጥ በመስመር እና በአጥቂ አማካይነት እየተጫወተ የሚገኘው ዋሊድ ሱሌይማን እና በ2016 ክለቡን የተቀላቀለው የፊት አጥቂ ማርዋን ሞህሰን በነገው ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ናቸው።