ከፍተኛ ሊግ ሀ | ለገጣፎ በምርጥ አጀማመሩ ሲቀጥል ሰበታ እና ፌዴራል ፖሊስም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሁሉም የአምሰተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሰበታ ከተማ እና ፌደራል ፖሊስ ድል ማስመዝገብ ችለዋል።

ለገጣፎ ላይ በሰንጠረዡ አናት የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲ እና ወልዲያን ያገናኘው ጨዋታ በለገጣፎ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።  ጨዋታው መጀመር ካለበት ሰዓት የፀጥታ ኃይል በስፍራው በሰዓቱ ባለመገኘቱ ምክንያት ለ17 ያህል ደቂቃዎች ዘግይቶ የተጀመረ ሲሆን  በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድን በኩል የነበረው አላስፈላጊ የአካል ንክኪ የጨዋታውን ውበት ቀንሶት ታይቷል። በሁለቱም በኩል ኳስን በረጅሙ ወደፊት ከማሻገር ያለፈ እንቅስቃሴ ሳይታይ ቆይቶ በ18ኛው ደቂቃ ወልድያዎች የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚን ዐቢይ ቡልቲ ከርቀት አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ በወጣበት ሙከራ መፍጠር ችለዋል። ከዚች ሙከራ በኋላ ሁለቱም ቡድን ኳስን ይዘው ለመጫወት የሚደርጉት ጥረት ባልተገባ አጫዋወት ቶሎ ቶሎ ሲቆራረጥ ነበር።

በለገጣፎ በኩል የአጭር ኳስ ቅብብሉን በመተው  በቀኝ መስመር በማድላት ሐብታሙ ፍቃደ ከመስመር በሚሻግረው እና ይዞት በሚገባው ኳሶች ወልድያን ለመፈትን ሞከረዋል። በዚህም አጨዋወት በ35ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ተማም በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ የግብ ጠባቂው ስህተት ታክሎበት ያገኘው ኳስ በግንባሩ ገጭቶት የግቡ ግራ አግዳሚ ለትሙ ወጥቶበታል። ተጋጣሚው ወልድያ በተደጋጋሚ ወደፊት ቢጠጉም ፍሬው ብርሃን እንዲሁም ይግርማቸው ተስፋዬ ካደረጉት የግብ ሙከራ ሌላ ምንም አይነት ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል። ለገጣፎ ከተማዋች በ41ኛው ደቂቃ አንዋር አብዱልጀባል በግምት 25 ሜትር አክርሮ የመታው ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ቅጣት ምት በሱፍቃድ ነገሽ በግሩም ሁኔታ መትቶ ግብ ጠባቂው ከላበት ሳይንቀሳቀስ ኳስን ከመረብ አገናኝቶ የመጀመርያው አጋማሽ በለገጣፎ መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብርቱ የመሸናነፍ ፉክክር እና በርካታ የግብ ሙከራ ተስተውሉበታል። በነፋሻነቱ የሚታወቀው የለገጣፎ ሜዳ ለተጋጣሚው ወልዲያ ማስቸገሩ በግልፅ የሚታይም ነበር። ኳስን ከግብ በመመስረት ወደ ሁለቱም የመስመር ተጫዋቾች በመበተን ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ለገጣፎዎች በ48ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ተማም ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ከፍያለው ኃይሉ ያዳነበት ሙከራ ጥሩ የግብ እድል ነበር። ወልዲያዎች ውጤቱን ለመቀልበስ ከዕረፍት መልስ ተጭነው ለመጫወት ሲሞከሩ በተለይም ተቀይሮ የገባው እንድሪስ ሰይድ ኳስን በማደራጀትም ሆነ የግብ ሙከራን በማድረግ ልቆ ወጥቶ ነበር። በ51ኛው ደቂቃ ከርቀት መትቶ በግቡ አናት የሄድችበት እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ መትቶ የለገጣፎ ግብ ጠባቂ አንተነህ ሐብቱ በጥሩ ሁኔታ ያዳነበት የሚጠቀሱ ናቸው ።

ወደ ኋላ አፈግፍጎ መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉት ለገጣፎዎች አልፎ አልፎ ወደፊት በሚጣል ኳስ የግብ እድሎች ቢፈጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በተለይም በ77ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ፍቃደ በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ ሮጦ ቢደርስም ተረጋግቶ ባለመምታቱ ኳሷ በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይሰተናግድበት በለገጣፎ መሪነት ተጠናቋል። በቀድሞ ምክትል አሰልጣኝ ዳዊት የሚሰለጥነው ለገጣፎ በአምስት ጨዋታ 13 ነጥቦች በመሰብሰብ ምድቡን መምራት ላይ ይገኛል::

በሌሎች ጨዋታዎች ሰበታ ላይ ሰበታ ከተማ አውስኮድን በ7ኛው ደቂቃ አቤል ታሪኩ፣ በ21ኛው ደቂቃ ኢብራሂም ከድር ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 አሸንፏል። ወደ ዱከም ያመራው ፌዴራል ፖሊስ ገላን ከተማን 2-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል። ሰይፉ ዘኪር በ27ኛው ደቂቃ ፖሊስን ቀዳሚ ሲያደርግ በሁለተኛው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ሰይፈ መገርሳ ሁለተኛውን አክሏል።

ኒያላ ሜዳ ላይ አቃቂ ቃሊቲ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማ ከአክሱም ከተማ እንዲሁም ደሴ ላይ ደሴ ከተማ ከወሎ ኮምቦልቻ ያደረጓቸው ጨዋታዎች በተመሳሳይ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።