ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪምየር ሊግ ዛሬ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደበት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻ በመከላከያ ሽንፈት ካስተናገደበት ስብስብ ውስጥ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ውብሸት ዓለማየሁን በተክሉ ታፈሰ ፣ አብዱልሰመድ ዓሊን በኄኖክ ኢሳይያስ እና እዮብ ዓለማየሁን በፀጋዬ አበራ በመተካት ወደ ሜዳ ገብቷል። እንግዳው ቡድን ድሬዳዋ ከነማ ደግሞ በተስተካካይ መርሐ ግብሩ ከደቡብ ፖሊስ አቻ ከተለያየበት አሰላለፍ ውስጥ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ብቻ በማድረግ ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋን በፍሬዘር ጌታሁን እንዲሁም ሲላ አብዱላሂን በሚኪያስ ግርማ ተክቷቸዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ብዙም ማራኪ ያልነበረ እና አልፎ አልፎ ድሬዳዋ ከተማዎች ኳሱን ለመቆጣጠር ከሚያረጉት እንቅስቃሴ  ድቻዎችም በሁለቱ የመስመር አጥቂዎቻቸው በመታገዝ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጪ ብዙም ቅርፁ ያልታወቀ  ነበር። ነገር ግን በዚህ ሂደት ወስጥም ነበር የዕለቱ ሁለት ግቦች የተስተናገዱት።

በ10ኛው ደቂቃ ኄኖክ ኢሳያስ በግራ የሜዳው ክፍል በኩል በረጅሙ የጣላትን ኳስ አንተነህ ተስፋዬ በግንባሩ ከጎል ክልሉ ለማራቅ ሲሞክር ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፀጋዬ አበራ ተረጋጋቶ በግሩም ሁኔታ መሬት ለመሬት በመምታት የጎሉ ግራ ጠርዝ ላይ አሰርፏታል። በጎሉ መቆጠር ምክንያት ወደ ጨዋታው በቶሎ ለመመለስ ድሬዳዋ ከተማዎች ከድቻ በተሻለ መልኩ መሀል ሜዳውን በበላይነት ለመያዝ ሲጥሩ ተስተውለዋል። በአንፃሩ ድቻዎች መሀል ሜዳ ላይ የሚያደርጉት ቅብብል በተደጋጋሚ በመቆራረጡ ምክንያት በቀላሉ ድሬዎች ኳስን በመቀማት በብቸኝነት የድቻን ተከላካይ ክፍል ሲፈትን ለነበረው አጥቅያቸው ኢታሙና ኬይሙኔ ሲያሻግሩ ነበር። በዚህም ሂደት ነበር በ16ኛው ደቂቃ ኄኖክ ኢሳይያስ ከበረከት ወልዴ እግር ስር በመውሰድ ለኄኖክ አርፊጮ ለመስጠት በሚጥርበት ወቅት ኳሷ በመንጠሯ ምክንያት ከሳጥን ውጪ ለነበረው ረመዳን ናስር ደርሳው አጥቂው ለመሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት በሜዳው ወጣ ገባነት በመታገዝ ከታሪክ ጌትነት መረብ ላይ አሳርፏታል። 

ከጎሏ መቆጠር በኃላም ድሬዳዋ ከተማዎች ከድቻ በተሻለ ጨዋታው ላይ መነቃቃትን ሲያሳዩ በተደጋጋሚ የቅጣት ምት ሲይገኙም ተስተውሏል። በዚህም ሂደት በ24ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችውን ቅጣት ምት ሳሙኤል ዮሃንስ በግሩም ሁኔታ በመምታት የግቡን የውስጠኛውን ብረት በመግጨት መስመር ያለፈች በሚመስል መልኩ ብታርፍም የድቻ ተከላካዮች እንደምንም አውጥተዋታል። ይህቺ ሙከራ የድሬዳዋ ከተማ የቡድን አባላትን ስታጨቃጭቅም ነበር። ድቻዎች ከ35ኛው ደቂቃ በኃላ ድቻዎች በቸርነት ጉግሳ ፣ እሸቱ መና እና በፀጋዬ አበራ አማካኝነት ወደ ቀኝ ባመዘነ መልኩ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ይህም ጫና ቀጥሎ በ44ኛው ደቂቃ ከቸርነት ጉግሳ የተቀበለውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት ወደ ወጪ የወጣበት አጋጣሚ ይጠቀሳል። 

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ከመጀመርያው በተሻለ ፉክክር የታየበት  እና ግልፁ የሆኑ የጎል አጋጣሚዎች የተፈጠሩበት ነበር። ድሬዎች በይበልጥ ለማጥቃት ከዕረፍት ሲመለሱ ሐብታሙ ወልዴን በኃይሌ እሸቱ በመተካት እና ኢታሙና ኬይሙኒን ወደ ግራ በማስወጣት የጨዋታ ቅርፅ ለውጥ ቢያደርጉም ግልጽ የሆነ የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም ነበር። በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ሦስቱን ነጥቦች ለማገኘት ጠንከር ያለ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በ47ው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተላከችውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ኄኖክ ኢሳያስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አስቆጠረ ሲባል በሚያስቆጭ መልኩ ለግብ ጠባቂው  ፍሬዘር ጌታሁን አስይዞታል። የድሬዳዋ ከተማ የጨዋታ እንቅስቃሴ በይበልጥ ከተከላካይ እና አማካይ የሜዳ ክፍሎች የተገደበ ሲሆን ብዙም ጫና ሲፈጥሩ አልተስተዋሉም ።

ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሳሀ ያደረግጓቸው ለውጦች በተደጋጋሚ ጫና ለመፍጠር የረዳው ይመስላል በተለይም እዮብ አለማየው ወደ ሜዳ ከገባ ጀምሮ የነበረው እንቅስቃሴ በአመዛኙ በግራ መስመር ጥቃት እንዲሰነዝሩ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በ65ኛው ደቂቃ በዚሁ ሂደት የተገኘችውን ኳስ ኄኖክ አረፊጮ አግኝቶ ሲመታ ወደ ውጪ ሲወጣበት በ67ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተላከችውን ኳስ ፀጋዬ አበራ በግንባሩ ቢሞክርም ለጥቂት ኢላማውን ሳይመታ ቀርቷል።

ከ75ኛው ደቂቃ በኃላ የነበረው የጨዋታ ሂደት በድቻ ጥሩ የኳስ ፍሰት የታጀበ ቢሆንም ለጎል የሚሆኑ ዕድሎች ግን መፈጠር አልቻሉም። በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ነጥብ ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ በተደጋጋሚ ሲወድቁ የነበረ ሲሆን ይሄም ድርጊት አብዛኛውን ስታድየም ውስጥ የነበረ ተመልካች ቁጣ ሲቀሰቅስም ተስተውሏል። ጨዋታውም በዚህ መልኩ ሲቀጥል በ83ኛው ደቂቃ ላይ ኢታሙና ኬይሙኒ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ለማግኘት ጥረት በሚያደርግበት ሂደት ውስጥ ተክሉ ታፈሰ የጨረፋት ኳስ ከጎሉ ወጣ ብሎ የቆመው ታሪክ ጌትነት እንደምንም በጣቱ በመንካት ከግቡ አግዳሚ በላይ አውጥቷታል። ጨዋታው ሰባት ደቂቃዎች የተጨመሩበት ቢሆንም ምንም ዓይነት ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

የእለቱ ዳኛ የነበሩት ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ጨዋታው የከበዳቸው በሚመስል መልኩ ከረዳቶቻቸው ጋር በተደጋጋሚ የተቃረነ ውሳኔም ሲወስኑ ተመልክተናል ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ተመልካቹም ከሜዳ መውጣት በጀመረበት ቅጽበት የድሬዳዋ ከተማው ኢታሙና ኬይሙኒ የድቻው ተከላካይ ሙባረክ ሽኩርን በቡጢ በመነረቱ በተፈጠረው ግርግር መነሻነት የተነሳው የደጋፊዎች ግርግር አስለቃሽ ጭስ እስከማስተኮስ ደርሷል። እንደ ድሬዳዋ የፌስ ቡክ ገፅ ከሆነም የክለቡ አውቶብስ መስታወት መሰበሩ እና ሹፌሩ ላይም ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።