” የጨዋታዎች መደራረብ ነው ለጉዳት የዳረገኝ ” ቢኒያም በላይ

በአልባኒያ ለስኬንደርቡ ኮርሲ እየተጫወተ የሚገኘው ኢትዮጵያው አማካይ ቢኒያም በላይ በገጠመው ጉዳት ምክንያት በቅርብ የክለቡ ጨዋታዎች ላይ እየታየ አይገኝም።

በ2009 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለቆ ወደ ጀርመን በማምራት በተለያዩ ክለቦች ሙከራን ሲያደርግ ከቆየ በኋላ የአልባኒያው ስከንደርቡ ኮርሲን ከስኬታማ የሙከራ ጊዜ በኋላ በሦስት ዓመት ውል የተቀላቀለው ቢኒያም በ2018/19 የውድድር ዘመን የመጀመሪያው አጋማሽ በ17 የሊግ እና የዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈ ሲሆን ሊጉ ለእረፍት ከመቋረጡ በፊት በእግሩ ላይ ጉዳት በገጠመው ጉዳት ከሜዳ ርቋል። ተጫዋቹ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታም የጉዳቱ መንስዔ የጨዋታ መደራረብ እንደሆነ ተናግሯል። ” በሊጉ እየተጫወትኩ ባለሁበት ሰዓት ነው የተጎዳሁት። ከሜዳ ከራቅኩም ትንሽ ቆየው፤ በተደጋጋሚ በቋሚነት ለቡድኔና ለሀገሬ በመጫወቴ የጨዋታ መደራረብ ነው ለጉዳቴ ምክንያት የሆነኝ ” ብሏል።

ካለፈው የውድድር ዓመት ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት የቡድኑ መደበኛ ተሰላፊ የሆነው ቢኒያም ወደ ሜዳ ለመመለስ አንድ ወር ያህል ጊዜ እንደሚወስድበት ሲል ሀሳቡን ይቀጥላል “እረፍት በሚገባ ያስፈልገኛል። የውድድሩ አንደኛው ዙር ተጠናቆ እረፍት ላይ ነበርን። ቡድኑ በዚህ ሰዓት ለሁለተኛው ዙር ዝግጁቱን ጀምሯል። እኔ ግን ወደ ሜዳ ለመመለስ ቢያንስ አንድ ወር ይቀረኛል። ክለቤ ስከንደርቡ በሚገባ እየተከታተለኝ ነው፤ ህክምናውም ጥሩ ነው። በቻሉት መጠንም እየረዱኝ ነው። በርግጠኝነት ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜም በቅርቡ እመለሳለሁ ብዬ አስባለሁ።”

የሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ከ15 ቀን በኋላ እንደሚጀምር በሚጠበቀው የአልባኒያ ሱፐርሊጋ የአምናው ቻምፒዮን ስከንደርቡ ከመሪው ፓርቲዛኒ በ7 ነጥቦች ርቆ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከክለቡ ጋር የአንድ ዓመት ውል የሚቀረው ቢኒያም የተሻለ ክለብ ካገኘም በዛው አልባኒያ አልያም ወደ ሌላ አውሮፓ ሀገር ሊሄድ እንደሚችል በቆይታው ተናግሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *