ሽመልስ በቀለ በመጀመርያ ጨዋታው አዲሱ ቡድኑን ታድጓል

ከሁለት ቀናት በፊት ሶስት ዓመታት የተጫወተበት ፔትሮጀትን ለቆ ወደ ሌላው የግብፅ ክለብ ምስር ኤል ማቃሳ ያመራው ሽመልስ በቀለ ዛሬ በመጀመሪያ ጨዋታው ሁለት ግቦች በማስቆጠር ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ድል እንዲያደርግ ረድቷል

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ምስር ኤል ማቃሳ በአረብ ኮንትራክተርስ ስታድየም አል ሞካውሉን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል። ማቃሳዎች 31ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ ሰሚር ለአል ሞካውሉን በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ እየተመሩ ወደ ዕረፍት ቢያመሩም በ57ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በመግባት የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገው ሽመልስ በቀለ ግብ ለማስቆጠር የፈጀበት ጊዜ ሰባት ደቂቃ ብቻ ነበር።

በ64ኛው ደቂቃ የአቻነቱን እና በ90ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ በማስቆጠር ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ አሸንፎ እንዲወጣ ቁልፍ ሚና ተወጥቷል። በፔትሮጀት ሰባት ጎሎች የነበሩት ሽመልስ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ ዘጠኝ በማሳደግም በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ተርታ መመደብ ችሏል።

ምስር ኤል ማቃሳም በድሉ በመታገዝ ደረጃውን ወደ ሦስተኛነት ሲያድግ በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎቹ ታላላቆቹ አል አህሊ እና ዛማሌክን ይገጥማል።

በተያያዘ መረጃ የሌላው ኢትዮጵያዊ ዑመድ ኡኩሪ የሚጫወትበት ስሞሀ ዛሬ ምሽት ከሜዳው ውጪ ከናጉም ጋር ይጫወታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *