ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ባህርዳር ከተማ

ከነገ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ወልዋሎ ባህርዳርን የሚያስተናግድበት ጨዋታ የቅድመ ዳሰሳችን የመጀመሪያ ትኩረት ይሆናል።

በዘጠነኛው ሳምንት በትግራይ እና አማራ ክልል ክለቦች መካከል የተደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ ያስተናገደው ወልዋሎ ዓ/ዩ ነገ ደግሞ ባህር ዳር ከተማን ይቀበላል። ከሰባተኛው ሳምንት በኋላ ወደ አሸናፊነት መመለስ የከበዳቸው ወልዋሎዎች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከአንድ ነጥብ በላይ ማሳካት አልቻሉም። እስካሁን በሊጉ ሁሉንም ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን በ13 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሯቸው ባህር ዳሮች በበኩላቸው ከተጋጣሚያቸው አራት ደረጃዎችን ከፍ ብለው ይገኛሉ። በስምንተኛው እና ዘጠነኛው ሳምንት አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካት የታየባቸውን መቀዛቀዝም ባሳለፍነው ቅዳሜ ደደቢትን 2-0 በመርታት መቀልበስ ችለዋል። ነገም ለሁለተኛ ጊዜ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ እንደሚጥሩ ሲጠበቅ ወልዋሎም ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።

የወልዋሎ ዓ/ዩዎቹ ዳንኤል አድሓኖም ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው አስራት መገርሳ ደግሞ በጅማው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት ከነገው ጨዋታ ሙጪ ሆነዋል። ባህር ዳር ደግሞ በ10ኛው ሳምንት ደደቢትን ሲረታ 78ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት የገጠመው ዳንኤል ኃይሉ ለነገው ጨዋታ አይደርስም። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ሙሉ ስብስቡን ይዞ ወደ መቐሌ አምርቷል።

ከአሸናፊነት መራቁ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ላይ ጫና እያሳደረ የሚገኘው ወልዋሎ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ ሊኖረው ቢችልም ጥንቃቄ የሚለየው አይመስልም። ቡድኑ በተለይም አማካይ ክፍል ላይ ያለው ምርጫው መመናመን መሀል ሜዳ ላይ ለሚጠብቀው ፍልሚያ የመስመር አጥቂዎቹን ተሳትፎ በእጅጉ ይፈልጋል። በተቃራኒው ከዳንኤል ጉዳት ውጪ የመጀመሪያ ተመራጭ የነበሩትን ተጫዋቾችን ያገኘው ባህር ዳር በጠንካራው የኋላ መስመሩ የባለሜዳዎቹን ጥቃት ለመመከት የመስመር ተከላካዮቹን ሜዳው ላይ በማቆየት እንደሚጫወት ይጠበቃል። በማጥቃቱ በኩል ግን መሀል ሜዳ ላይ ያለውን ፍልሚያ ማሸነፍ ከቻለ በግርማ እና ወሰኑ በኩል ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል መግባትን ዋነኛ ምርጫው ሊያደርግ ይችላል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በ2009 በከፍተኛ ሊጉ ከተገናኙ በኋላ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

– ወልዋሎ ዓ/ዩ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን አንድ ብቻ ሲሆን ያሳካቸው ሦስት ነጥቦችም ከአቻ ውጤቶች የተገኙ ነበሩ። ቡድኑ ትግራይ ስታድየም ላይ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች መካከል በአንዱ ብቻ ድል ቀንቶታል።

– ከአራት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን መሰብሰብ የቻሉት ባህር ዳሮች እስካሁን ግብ ሳያስቆጥሩ የወጡት በሀዋሳ ጋር ያለግብ በተለያዩበት ጨዋታ ብቻ ነው።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በሦስት ጨዋታዎች 16 የቢጫ ካርዶችን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

አማኑኤል ጎበና – ብርሀኑ አሻሞ – አፈወርቅ ኃይሉ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት አሎ

ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ደረጄ መንግስቱ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ

ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት – ግርማ ዲሳሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *