ሊዲያ ታፈሰ እና ተመስገን ሳሙኤል በሁለት ውድድሮች ላይ እንዲመሩ ተመርጠዋል

ኢትዮጵያዊያኑ ኢንተርናሽናል ዳኞች ሊዲያ ታፈሰ (ዋና) እና ተመስገን ሣሙኤል (ረዳት) ፖርቱጋል እና ኒጀር ላይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ እንዲዳኙ መመረጣቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል። 

በፖርቱጋል አስተናጋጅነት የሚከሄደውና 12 ሴት ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት አልጋርቭ ዋንጫ  ከፌብሪዋሪ 27 እሰከ ማርች 06 ቀን 2019 የሚከናወን ሲሆን ፊፋ ከስድስቱ ኮንፌዴሬሽኖች ውስጥ ከተመደቡት ዋና ዳኞች መካከል ከካፍ ሊዲያ ታፈሰን እንዳካተተ ገልጿል። ሊዲያ በቅርቡ ተካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የመክፈቻ እና ወሳኝ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች የመራች ሲሆን በፈረንሳይ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ሴቶች ዋንጫ ላይ እንዲመሩ ከተመረጡ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ መካተቷ የሚታወስ ነው። 


በኒጀር አስተናጋጅነት ከፌብሩዋሪ 2 እስከ 17 ቀን 2019 በሚካሄደው ቶታል ካፍ ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በዳኝነት እንዲመራ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሣሙኤል ተመርጧል። ተመስገን በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአፍሪካ እና ዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች እና የክለብ ውድድሮች በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሲመደብ የቆየ ሲሆን የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምስጉን ረዳት ዳኛ ሆኖ መመረጥ ችሏል። ተመስገን በኒጀሩ ውድድር ከኢትዮጵያ በብቸኝነት የተመረጠ ዳኛም ሆኗል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *