ጋቶች ፓኖም በኤል ጎውና ማልያ የመጀመርያ የሊግ ጎሉን አስቆጠረ

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ኤል ጎውና ከሜዳው ውጪ ሀራስ ኤል ሁዳድን 2-1 ሲያሸንፍ ኢትዮጵያዊው አማካይ ጋቶች ፓኖም የመጀመርያ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል።

አሌክሳንድሪያ ላይ በተካሄደው ጨዋታ እንግዶቹ ኤል ጎውናዎች በጋቶች ፓኖም የ36ኛ ደቂቃ ጎል ቀዳሚ በመሆን ወደ እረፍት ሲያመሩ ኤል ሑዳዶች ኢብራሂም ኮኔ ከእረፍት እንደገቡ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል። ከ7 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አህመድ መኪ ኤል ጎውናን ወደ ድል የመራች ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በእንዳው ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል። በድሉ ተጠቅሞም ኤል ጎውና በ22 ነጥቦች ደረጃውን ወደ 10ኛ አሻሽሏል።

 

የጨዋታውን ቀዳሚ ጎል ያስቆጠረው ጋቶች ፓኖም መቐለን ለቆ ወደ ክለቡ በዓመቱ መጀመርያ ካመራ በኋላ በ17 የሊግ ጨዋታዎች የተሰለፈ ሲሆን በ18ኛው ጨዋታ የመጀመርያ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል።

በሊጉ 20 ሳምንት ጨዋታ ከደቂቃዎች በኋላ ዑመድ ኡኩሪ የሚገኝበት ስሞሀ ከኤንፒ ጋር ከሜዳው ውጪ ሲጫወት በአዲሱ ክለቡ በመጀመርያ ጨዋታው ድንቅ አጀማመር ያደረገው ሽመልስ በቀለ የሚጫወትበት ምስር ኤል ማቃሳ ነገ 12:00 አል አህሊን ያስተናግዳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *