ተመስገን ካስትሮ ለወራት ከሜዳ ይርቃል

ከአርባምጭ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ዘንድሮ በመቀላቀል መልካም የሚባል የውድድር ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ተከላካዩ ተመስገን ካስትሮ በገጠመው ጉዳት ለወራት ከሜዳ ይርቃል።

በ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትላንት አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ጅማ አባጅፋርን የገጠሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች የቀድሞው ተጫዋቻቸው አስቻለው ግርማ በ63ኛው ደቂቃ በተቆጠረባቸው ብቸኛ ግብ በሜዳቸው የ1-0 ሽንፈት ሲያስተናግዱ በጨዋታው ተመስገን ካስትሮ በ15ኛው ደቂቃ ላይ የጉልበት ጉዳት ገጥሞታል። ጉዳቱም በሜዳ ላይ ህክምና ብቻ በቂ አለመሆኑን ተከትሎ ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል ለተጨማሪ ህክምና በፍጥነት ማምራቱም ይታወቃል። የክለቡ የህክምና ባለሙያ የሆነው ይስሐቅ ሽፈራው የተመስገን ካስትሮ የጉዳት ሁኔታ እና መጠን እንዲሁም ከጉዳቱ አገግሞ መቼ ወደ ሜዳ ይመለሳል ለሚለው ጥያቄያችን ይህን ምላሽ ሰተውናል።

” ቤተዛታ በመውሰድ ኤምአርአይ አስነስተናዋል። የጉልበት ውልቃት እና ሁለቱ የጡንቻዎቹ ጅማቶች የመሰንጠቅ ጉዳት አጋጥሞታል። ከጉዳቱ ለማገገም ብቻ ስምንት ሳምንት ይወስዳል። ወደ ሜዳ ላይ ልምምድ ለመጀመር አንድ ወር ቢፈጅበት በአጠቃላይ ወደ ጨዋታ ለመመለስ አስከ አራት ወር የሚቆይ ረዘም ያለ ጊዜ ይፈጃል ” ብለውናል።

በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በተጫዋቾች ጉዳት እየታመሰ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ወሳኙን የቡድኑ ተከላካይ ተመስገን ካስትሮን ለወራት ከሜዳ ማጣት የተከላካይ መስመሩን እንዳያሳሳበት ያሰጋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *