“አሁን ድኛለሁ” – ሄኖክ አየለ በፈተና ከተሞላ የእግርኳስ ህይወቱ ዳግም አንሰራርቷል

” ጉዳቴ ካሰብኩበት እንዳልደርስ ፈተና ሆኖብኝ ቆይቷል”

– ካለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ አራቱን በጉዳት አሳልፏል፡፡

በአዲሱ ሚሌንየም መጀመርያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ብቅ ብለው ተስፋ ከተጣልባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኖ ነበር። ነገር ግን መልካም አጀማመሩ በተደጋጋሚ ጉዳቶች ተጨናግፎ በአሳዛኝ መልኩ ያሰበበት እንዳይደርስ አድርጎታል። የእግርኳስ ህይወቱ በተስፋ አስቆራጭ ሁነቶች የተሞላ ቢሆንም በተደጋጋሚ ከወደቀበት እየተነሳ የሚወደውን እግርኳስ መጫወቱን አላቆመም። አሁን በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው የደቡበ ፖሊሱ አጥቂ ሄኖክ አየለ ስለ እግር ኳስ ህይወቱ፤ በጉዳት ስላሳለፋቸው ዓመታት እና አሁን ስላለበት ሁኔታ ከቴዎድሮስ ታከለ ጋር ቆይታ አድርጓል። 

“እግር ኳስን መጫወት የልጅነት ህልሜ ነበር። ” የሚለው ሄኖክ በ1997 በታዳጊ በፕሮጀክት ቡድን በመታቀፍ የጀመረው ጉዞው ወደ ክለብ እግርኳስ ለመሸጋገር ብዙ ጊዜያት አልፈጀበትም። በዛው ዓመት ክረምት ላይ ሀዋሳ ከተማ ቢ ቡድን ሙከራ አድርጎ ሳይሳካለት ቢቀርም በወቅቱ የብሔራዊ ሊግ ተሳታፊ የነበረው ደቡብ ፖሊስን መቀላቀል ቻለ። ” አሰልጣኝ ዘላለም ሺፈራው በሀዋሳ እንዳልተሳካልኝ ሲሰማ እኔ ጋር ስራ ብሎ አስጀመረኝ። ሌሎች ተጫዋቾች ካምፕ ሲያድሩ እኔ ከቤት እየተመላለስኩ ከክለቡ ጋር ስሰራ ከቆየሁ በኋላ አንደኛው ዙር ውድድርን ጨርሰው ልክ ወደ ሁለተኛው ዙር ሲገቡ አሰልጣኝ ዘላለም አዲስ አበባ ቡድኑ ለጨዋታ ሲሄድ አብሬያቸው እንድሄድ፤ በዛውም ፌዴሬሽን ገብቼ እንድፈርም አድርጎኝ ተሴራ ወጣልኝ።  የእግር ኳስ ህይወቴንም በክለብ ደረጃ በመጫወት ጀመርኩ። ይህ የሆነው 1999 ግማሽ ዓመት ላይ ነበር። ” ሲል የክለብ ህይወት አጀማመሩን ያስታውሳል።

ደቡብ ፖሊስ በ1999 የብሔራዊ ሊግ ቻምፒዮን ሆኖ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ የቡድኑ አባል የነበረው ሄኖክ እስከ 2002 በነበረው የክለቡ የሊግ ቆይታ አብሮ መቆየት ችሏል። ከደቡብ ፖሊስ ወደ ብሔራዊ ሊግ ተመልሶ መውረድ በኋላ ቀጣይ የሄኖክ ማረፊያ የሆነው ሌላው የፕሪምየር ሊግ ክለብ የሆነው አዳማ ከተማ ሆነ። የሄኖክ እጅግ ፈታኝ ጊዜያት መጀመርያ የተከሰተውም በአዳማ ነበር። ” በታኅሣሥ ወር በጉልበቴ ላይ ጉዳት ገጠመኝ። የዛን ወቅት ትንንሽ ህክምናዎችን ካደረኩ በኋላ በድጋሚ መጫወት ጀምሬ በአዳማ ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ በአሰልጣኝ ቶም ሴንትፌይት ለብሔራዊ ቡድን እንድመረጥ አስችሎኝ ነበር። ለብሔራዊ ቡድኑ አዳማ ላይ ዝግጅት ስናደርግ ግን በድጋሚ ያመኝ የነበረውን ጉልበቴን ተመታሁና ከብሔራዊ ቡድን ውጪ ሆንኩ። ” የሚለው ሄኖክ የአዳማ ቆይታው በሜዳ ላይ ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ እስከ ብሔራዊ ቡድን ቢያደርሰውም ጉዳት ግን ጉዞውን ገትቶበታል። ሄኖክ የአዳማ ጥሩ ብቃቱን ተከትሎ ወደ ሲዳማ ቡና አምርቶ የነበረ ቢሆንም በብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ወቅት በገጠመው ጉዳት ምክንያት በአዲሱ ክለቡ ጨዋታ ለማድረግ ረጅም ጊዜያት ፈጅቶበታል። ” የገጠመኝ ጉዳት ከባድ በመሆኑ በ2004 ሙሉውን ዓመት ሳልጫወት አሳለፍኩ፡፡ በ2005 ግን በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ሲዳማ ቡናን አገልግያለሁ። ” ሲል በሲዳማ የነበረውን ጊዜ ይገልፃል።

የሲዳማ ቡና ቆይታውን ከደመደመ በኋላ በመቀጠል ማረፊያው ያደረገው የቀድሞ ክለቡ አዳማ ከተማን ነበር። በ2005 ከሊጉ የወረደው ክለቡ በ2006 በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መሪነት የብሔራዊ ሊግ ቻምፒዮን ሆኖ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲመለስ የሄኖክ እና ጓደኞቹ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር። በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ላይ ግን በድጋሚ ሄኖክ እና ጉዳት ተገናኙ። ሙሉ ለሙሉ መታከም እንዳለበት በማመንም ጉልበቱ ላይ ቀዶ ጥገና በማድረጉ በዚህም ምክንያት ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከእግርኳስ ለመራቅ ተገደደ።
ከሁለት ዓመታት በኋላ በድጋሚ በድጋሚ ወደ እግር ኳስ ለመመለስ ወስኖ ወልቂጤ ከተማን የተቀላቀለው ሄኖክ በዛም እድለኛ አልነበረም። ለረጅም ጊዜ የሚያርቀው ጉዳት በወልቂጤም ተከትሎታል። ” ከናሽናል ሴሜንት ጋር ስንጫወት ጭንቅላቴን ተመትቼ የምላስ መዋጥ አደጋ ደርሰብኝ፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ምቱ ከባድ ስለነበር ጭንቅላቴ ውስጥ ደም ፈሶ ነበር። ያ ደግሞ ለአንድ ዓመት እንዳርፍ አስገድዶኛል። ”

ጉዳት አብዝቶ የፈተነው ሄኖክ ወድቆ የመነሳት ታሪክ ቀጥሎ በ2010 በድጋሚ ወደ እግርኳስ ተመለሰ። ዲላ ከተማ የተጫዋቹን ግልጋሎት በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ማግኘት ከጀመረ በኋላ የእግርኳስ ህይወቱ በአዲስ መልክ አንሰራርቷል። በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቡድን ተጽዕኖ ለመፍጠር ጊዜ ያልፈጀበት አጥቂው በግማሽ ዓመት ቆይታው ቡድኑን የታደጉ ወሳኝ ስድስት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በተደጋጋሚ ሲጎበኘው የቆየው ጉዳቱም ፋታ የሰጠው ይመስላል።

በ2010 ደቡብ ፖሊስ በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ እየተመራ ከ8 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲመለስ በአዲሰ አሰልጣኝ እና በበርካታ የተጫዋቾች ለውጥ አዲሱን የውድድር ዘመን ጀምሯል። ሄኖክ አየለም የፕሪምየር ሊግ ጨዋታን “ሀ” ብሎ የጀመረበትን ክለብ በክረምቱ ተቀላቀለ። ” ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ በኋላ አሰልጣኝ ዘላለም ቡድኑን ሲይዝ ጠርቶኝ ጉዳትህ እንዴት ነው አለኝ፤ ጤንነቴን ማረጋገጥ ነበረበት። ጤነኛ በመሆኔ እና ሜዳ ላይ በማሳየው ነገር ደስተኛ በመሆኑ ለደቡብ ፖሊስ አስፈረመኝ። ” ሲል ወደ መጀመርያ ክለቡ የተመለሰበትን ሁኔታ ይገልፃል። እጅግ ደካማ የውድድር ዘመን በሊጉ እያሳለፈ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስ ከተጫዋቾቹም የሚፈለገውን አገልግሎት ማግኘት ባይችልም ሄኖክ በግል ጥረቱ ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል። በእስካሁኑ ጉዞውም በአራት ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው። ከስድስት ዓመታት በኋላ የተመለሰበተ ሊግም በጥሩ ሁኔታ የተቀበለው ይመስላል። ” ወደ ሊጉ ስመለስ በመጠኑም ቢሆን ግር ብሎኝ ነበር። በሂደት ግን ራሴን በማስተካከል ወደ ምርጡ አቋሜ መጥቻለሁ ባልልም የተሻለ እንቅስቃሴን በማድረግ ወደ ቀድሞ ብቃቴ በመመለስ ላይ እገኛለሁ፡፡ ” ይላል።

የእግርኳስ ህይወቱ ላይ ያለፉትን ውጣ ውረዶች ለተመለከተ ምን ያህል አስቸጋሪ ጊዜ እንዳሳለፈ መገመት ከባድ አይሆንም። ሄኖክም የገጠሙት ተደጋጋሚ ጉዳቶች ከራዕዮቹ እንዳሰናከሉት ነው የሚያምነው። “ጉዳቴ የከፋ ነበር፤ እንዲሁ በቀላሉ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም። ጉዳት በጣም ብዙ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል። የእኔ ራዕይ በጣም ሩቅ ነበር፤ ሆኖም ጉዳቴ ገሚሱ የጨዋታ ዓመታቴን በልቶብኛል ብዬ አስባለሁ። በትክክለኛ መንገድ ላይ እየተጓዝኩ ነበር። አዳማ እስክገባ ድረስም ጉዞዬ መልካም ነበር። ከዛ በኋላ የተፈጠረብኝ ጉዳት ወደኋላ አስቀርቶኛል፡፡ በሀገር ውስጥ ትልቅ ደረጃ በመድረስ ሀገሬን ለተሻለ ደረጃ አብቅቼ በውጭ ሀገራት ሊጎች የመጫወት ህልሜንም ገደል ከቶታል። ለስፖርተኛ የትኛውም አይነት ጉዳት ከባድ ነው። የጉልበት ሲሆን ደግሞ ይበልጡኑ ከባድ እንደመሆኑ ጉዳቴ ካሰብኩበት እንዳልደርስ ፈተና ሆኖብኝ ቆይቷል፡፡ ” ሲል ቁጭቱን ተናግሯል።

በእርግጥም ለእግርኳስ ተጫዋቾች ከባድ የሚባለው የጉልበት ጉዳት ነው። በርካቶችን ከሜዳ እስከወዲያኛው ቢያርቅም የቀድሞ ብቃታቸው በከፊል ወርዶ ወደ ጨዋታ የሚመለሱ ተጫዋቾችም አሉ። በሀገራችን ካለው በቂ ህክምና የማግኘት ዝቅተኛ እድል ጋር ሲደመርም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን ተስፋ አስቆርጦ ከእግርኳስ እንዲለዩ አድርጓቸዋል። ይህ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሄኖክ ላይም ነበር። ነገር ግን የእግርኳስ ፍቅሩ እና ጠንካራ ስራው መልሶ ተስፋ እንዲያደርግ እንደረዳው ይናገራል። “በጣም ተስፋ የቆረጥኩባቸው ወቅቶች ነበሩ። በጉዳቴ ወቅት ተመልሼ ኳስ ልጫወት ልጀምር ስል ኳስ መምታት እስኪያቅተኝ ድረስ ያመኝ ነበር። ነገ ላይ ቆሜ መራመድን እንኳ ቢከለክለኝስ? ብዬ የምጨነቅባቸው ወቅቶች ነበሩ። በጣም ከባድ ህመም ይሰማኝም ስለነበር በቃ ኳሱን አቁሜ ሌላ ስራን መስራት አለብኝ ብዬ የወሰንኩት ጊዜ ነበር፡፡ ኳስም ከመውደዴ የተነሳ ድጋሚ መስራት አለብኝ በማለት ተነሳስቼ ነው መስራትን የጀመርኩት።

” የሰው ልጅ ጠንክሮ ከሰራ የማያልፈው ነገር የለም ብዬ አምናለሁ። ለኔ በጉዳት ያሳለፍኳቸው ወቅቶች ከባድ ቢሆኑም ከዛ አስከፊ ጉዳቴ አገግሜ መጫወት ስጀምር ግን ጠንክሬ ከሰራሁ ወደነበርኩበት እንደምመለስ ራሴን አሳምኛለሁ፡፡ ያንንም ደግሞ በእርግጠኝነት እያሳካው ነው ብዬ አስባለሁ። ግን አሁንም በጣም የሚቀሩኝ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ በላይም መስራት እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ አንድ ሰው ጠንክሮ ከሰራ ምንም ነገርን ማለፍ ይችላል፡፡ ለምሳሌ እኔን ማንም ወደ እግርኳስ ይመለሳል ብሎ ያሰበ የለም። የፈጣሪ ፍቃድ ሆኖ ጠንክሬ በመስራቴ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እና ወደምወደው እግር ኳስ ልመለስ ችያለሁ፡፡ ማንም ሰው ከሰራ ችግሮችንና ጫናዎችን መቋቋም ከቻለ ስኬታማ መሆንም ይችላል፡፡ ”
አሁን ሄኖክ ቢያንስ ያለፉትን 12 ወራት ከጉዳት ርቆ የሚወደውን እግርኳስ እየተጫወተ ይገኛል። ከዚህ በኋላም ሁለት ጥያቄዎች በድጋሚ ከተወለደው ሄኖክን ምላሽ ማግኘትን ይሻሉ። ” በድጋሚ ጉዳት ይገጥመው ይሆን? በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ክለቡንስ በጎሎቹ ይታደገው ይሆን? የሚሉ… እነዚህ ጥያቄዎች በሜዳ ላይ ምላሽ የሚያገኙ ቢሆኑም ሄኖክ መልካም መልካሙን ተመኝቷል። ” ከዚህ በኃላ በሚኖሩን ጨዋታዎች ላይ ሁላችንም፤ በተለይም የመጀመርያ ተሰላፊዎች በጣም ጥሩ ከተጫወትን አሸናፊ የማንሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በግሌ ደግሞ መክፈል ያለብኝን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል ይኖርብኛል፡፡ እወጣዋለሁ የሚል እምነትም አለኝ። ከአሁን በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከህመሜ ነፃ ነኝ። ሰዎች ከአሁን አሁን እንዳያመው እያሉ ለኔ ይጨነቃሉ። እኔ ግን ያ ነገር ውስጤ የለም፤ ድኛለሁ። ” ይላል።

በመጨረሻም ተመልሶ እግርኳስን መጫወት እንዲችል እና በአስቸጋሪ ወቅቶች ሁሉ ከጎኑ የነበሩትን በማመስገን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ቆይታ ቋጭቷል። “በህክምናው በኩል ያገዙኝ፤ በተለይ ፊዚዮቴራፒስት ታምሩ ናሳን አመሰግናለሁ። “መጫወት ትችላለህ እያለ ይነግረኝ እና ህክምናዬን ይከታተልልኝ ነበር፤ ህክምና እያደረገልኝ አቅም አለህ በማለት በሥነ-ልቡናም እንድበረታ ያደርገኝ ነበር፡፡ ከዛ በተረፈ ጓደኞቼ ተመልሼ እግርኳስን እንደምጫወት፤ እንደሚሻለኝ ነበር ይነግሩኝ ነበር። ቤተሰቦቼንም ላመሰግን እፈልጋለሁ። በተለይ እናቴ እና ታናሽ ወንድሜ እርቅይሁን ባለፍኩባቸው ነገሮች ሁሉ ከጎኔ ነበሩ፡፡ ያበረቱኝ ያጠነክሩኝም ነበር ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *