ዮሐንስ ሳህሌ ወልዋሎን ለማሰልጠን ተስማሙ

ወልዋሎዎች አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ዋና አሰልጣኝ አድርገው ቀጥረዋል።

ባለፈው ሳምንት ክለቡ ለአንድ ዓመት በአሰልጣኝነት ከመሩት ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር በስምምነት የተለያዩት ቢጫ ለባሾቹ ዮሐንስ ሳህሌን አዲስ አሰልጣኝ አድርገው መሾማቸው ታውቋል። በዚህ ዓመት መጀመርያ ድሬዳዋ ከተማን ለማሰልጠን ተስማምተው ብዙም ሳይቆዩ ከቡድኑ በፍቃዳቸው የተለያዩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከደቂቃዎች በፊት ወልዋሎን ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ለማሰልጠን ሲስማሙ በዓመቱ መጨረሻ በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት ውላቸውን ሊያራዝሙ እንደሚችሉም የአሰልጣኙ ወኪል አክበረት ተመስገን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፃለች።

ከዚህ በፊት የወልዋሎ ተቀናቃኝ የሆነው መቐለ 70 እንደርታን ጨምሮ ድሬዳዋን እንዲሁም ደደቢትን በሁለት አጋጣሚዎች ማሰልጠን የቻሉት አሰልጣኝ ዮሐንስ የኢትዮጵያ ዋና ብሔራዊ ቡድን እና ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንንም በዋና አሰልጣኝነት የመሩ ሲሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በደደቢት በቴክኒክ ዳይሬክተርነት ማገልገላቸውም ይታወሳል።

አሰልጣኙ በሁለተኛው ዙር መጀመሪያ በትግራይ ስቴድየም ወልዋሎ ከሃዋሳ ከተማ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ቡድኑን መምራት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *