የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-1 ወላይታ ድቻ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ዛሬ በገለልተኛ ሜዳ (አዲስአበባ ስታዲየም) ላይ ሲዳማ ቡናን ከወላይታ ድቻ ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታ ተመጣጣኝ ነበር ፤ ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት ነበር ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም በአንደኛው ዙር ድቻን በእዚሁ በአዲስ አበባ ስታዲየም በገጠምንበት ጨዋታ እንደ ዛሬው ኳሱን ይዘው አልተጫወቱም። በዛሬው ጨዋታም እንደመጀመሪያው ዙር ሁሉ ረጃጅም ኳሶችን ምርጫቸው ያደርጋሉ ብለን ገምተን ነበር የመጣነው። ዞሮ ዞሮ ጨዋታው ጥሩ ነበር ለማለት ያስችላል፡፡”

ከሜዳቸው ውጪ መጫወታቸው ቡድኑ ላይ ስለፈጠረው ጫና እና ዳኝነት

“ምንም ጥርጥር የለውም ከሜዳ ውጪ ስትጫወት ጫና መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ስለዳኝነቱ ምንም ማለት ባልፈልግም ጫናዎች እየተፈጠሩብን ነው፡፡ ዳኞችን ተችቼ አላውቅም፤ ነገር ግን የዛሬው በጣም ያበሳጫል። በተለይም በቀኝ በኩል የነበረው የመስመር ዳኛ ብዙ ስህተቶቸችን ሲሰራ ነበር፡፡”

ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ተጫዋቾች ስለፈጠሩት ክፍተት

“ሐብታሙ ገዛኸኝ በአሁኑ ወቅት ቡድናችን ውስጥ አለን የምንለው አጥቂ ነው። የእሱ አለመኖር በተለይ በዛሬው ጨዋታ ላይ ክፍተት ፈጥሮብናል፡፡”

አሸናፊ በቀለ – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ላለመሸናነፍ ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር፤ ወራጅ ቀጠና እንደመገኘታችን ውጤቱ ያስፈልገን ነበር። በቀጣይ ደጋፊያችንን ይዘን የተሻለ ነገር ለመስራት እንጥራለን፡፡”

በገለልተኛ ሜዳ ስለመጫታቸው

“በገለልተኛ ሜዳ መጫወቱ በራሱ ጫና ላይፈጥር ይችላል፤ ነገርግን የደጋፊዎች ተፅዕኖ ሲታከልበት ልዩነት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም ለሁሉም ክለቦች እኩል ነው፤ በአዕምሮ ደረጃ ዝግጅት ስላደረግን ያን ያህል አልከበደንም፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *