የአሰልጣኞች አስተያየት | ደደቢት 1-0 ደቡብ ፖሊስ

በ18ኛ ሳምንተ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መክፈቻ ደደቢት በሜዳው ደቡብ ፖሊስን 1-0 ከረታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“የዛሬው ድል ይገባናል” ዳንኤል ፀሃዬ – ደደቢት

ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን አስበነው ነበር። ምክንያቱም ደቡብ ፖሊስ አራት ተከታታይ ጨዋታ አሸንፎ የመጣ ቡድን ነው። ሆኖም እኛ ምንፈልገው ሶስት ነጥብ ስለነበር እሱም አሳክተን መውጣት ችለናል። ደቡብ ፖሊስ እኛ አከባቢ (ወራጅ ቀጠና) ነው ያለው። ምንም እንኳ በነጥብ ብንለያይም። ስለዚህ በነጥብ የሚቀራረበንን ቡድን የግድ ማቆም ነበረብን። ከዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥብ መውሰዳችንም ትልቅ ነገር ነው።

ስለ ዛሬው ድል

የዛሬው ድል ይገባናል። ደቡብ ፖሊስ መጥፎ ቡድን አይደለም፤ ጥሩ ቡድን ነው። በሶስቱም የሜዳ ክፍሎች ጥሩ ናቸው። ሆኖም እኛ በተሻለ የግብ ዕድሎች ፈጥረናል። ከዚ በላይም ግብ አግብተን የምንወጣበት ዕድል ነበር። የመጀመርያው ግብ እንዳገባን ብዙም ሳንቆይ ሁለተኛ የማግባት ዕድል ነበረን። አንድ ለዜሮ መሆኑ እና ደደቢት ብዙ ሽንፈት ያስተናገደ ቡድን እንደመሆኑ ሶስት ነጥቧን ለመውሰ እኛም ተጫዋቾቻችንም ሶስት ነጥብ ችኩሎች ሆነን ነበርን። ሆኖም ነጥቡን ይዘን መውጣታችን ይገባናል።

“በሚቀጥለው ጨዋታ ወደነበረን ጥሩ ብቃት እንመለሳለን” ገብረክርስቶስ ቢራራ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታውን ስንጀምር ዝናብ ዘንቦ ሜዳው ኳስ ያንሸራትት ስለነበር ኳስ ለመቆጣጠር አስቸግሮን ነበር። ከዛ ውጭ ግን ጨዋታው ጥሩ ነበር።

ከባለፉት ጨዋታዎች አንፃር የቡድኑ ብቃት መውረድ

ይሄ በእግር ኳስ ላይ ያለ ጉዳይ ነው። በእንደዚ አይነት ፉክክር ነጥብ አስጥሎ መደራረስ ወሳኝ ስለሆነ፤ እኛ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ሆኖም ጎሉ ከገባ በኋላ በእነሱ በኩል ኳሱን በማቆየት እና ግዜ ማባከን ነበር። በኛ በኩል ችኮላ ነበር ፤ ከዛ በኃላ ያገኘናቸው ዕድሎች መጠቀም ስላልቻልን ተሸንፈናል፤ እንቀበለንም።

የዛሬ ውጤት በጥሩ ብቃት ላይ እያለን የመጣ መሆኑ ምንም ችግር አይፈጥርም። ይሄ እንደሚሆን እናውቅ ነበር፤፣ እግር ኳስ ውስጥ ሶስት ነገሮች አሉ፤ ሁልጊዜ ተጫዋቾቻችን ይህን ስለሚያውቁ የዛሬ ውጤት በቀጣይ ጨዋታዎች የሚያመጣብን ተፅዕኖ የለም ። በሚቀጥለው ሳምንት ወደነበረን ጥሩ ብቃት እንመለሳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *