ምድብ ለ | መድን እና ወልቂጤ ሲያሸንፉ ኢኮስኮ ነጥብ ጥሏል

15ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ጨዋታዎች እሁድ ሲካሄዱ መድን መሪነቱን ያስጠበቀበትን፤ ወልቂጤ ወደ ሁለተኛ ከፍ ያለበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

መድን ሜዳ ላይ አዲስ አበባ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ መድን 4-1 በማሸነፍ መሪነቱን አስጠብቋል። አብዱለጢፍ ሙራድ በ2ኛው እና በ44ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው ጎሎች መድን 2-0 እየመራ ወደ እረፍት ሲያመሩ በ47ኛው ደቂቃ ሚካኤል ለማ የመድንን ልዩነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ደግሞ አብዱለጢፍ ሙራድ ሐት-ትሪክ የሰራበትን የቡድኑን አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በምድቡ መሪ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወልቂጤ ላይ ወልቂጤ ከተማ ከሀላባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በ27ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ባገባው ብቸኛ ግብ ወልቂጤ 1-0 አሸንፏል። የኢኮስኮ ነጥብ መጣልን ተከትሎም ወልቂጤ ወደ ሁለተኛ ደረጃ መመለስ ችሏል።

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ፖሊስ ከኢኮስኮ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። በግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ፖሊሶች በ34ኛው ደቂቃ ላይ በፈርዓን ሰዒድ አማካይነት የነበረ ሲሆን የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ሄኖክ አወቀ ለኢኮስኮ ግብ አስቆጥሮ አቻ ሆነዋል። በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ድሬዎች በዘሪሁን ተስፋዬ ጎል በድጋሚ መሪ መሆን ቢችሉም በ62ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ጥጋቡ ኢኮስኮችን አቻ አድርጓል።

በሌሎች ጨዋታዋች ወደ ዲላ ያመራው ናሽናል ሴሜንት ባለሜዳው ዲላ ከተማን 1-0 ሲያሸንፍ ኦሜድላ ሜዳ ላይ የካ ክ/ከተማ ከሀምበሪቾ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል። አርሲ ነገሌ ላይ ነገሌ አርሲ ከ ወላይታ ሶዶ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ላይ ሳለ በከባድ ንፋስ ምክንያት ሳይጠናቀቅ ቀርቷል። ዛሬ ከደቂቃዎች በኋላም ከቆመበት እንደሚቀጥል ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡