ከፍተኛ ሊግ ሀ | መሪው ሰበታ ከተማ ከተከታዮቹ ያለውን ልዩነት መልሶ አስፍቷል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 15ኛ ሳምንት የምድብ ሀ ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ መሪነቱን ሲያጠናክር ለገጣፎ ነጥብ ጥሏል።

ሰበታ ከተማ በሜዳው ያለመሸነፍ ጉዞውን አጠናክሮ በቀጠለበት ጨዋታ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ 3-1 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። ፋሲል ከነማን በመልቀቅ ወደ ቀድሞ ክለቡ ዳግም የተቀላቀለውና ዘንድሮ ጥሩ አቋሙን እያሳየ የሚገኘው ናትናኤል ጋንቹላ በ25ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ሰበታዎች ቀዳሚ መሆን ሲችሉ ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ሐብታሙ ረጋሳ በቅጣት ምት ባስቆጠረው ጎል እንግዶቹ አቻ ሆነዋል። ወደ እረፍት ሊያመሩ አንድ ደቂቃ ሲቀር ደግሞ በድጋሚ ናትናኤል ጋንቹላ አስቆጥሮ ሰበታ 2-1 መምራት ችሏል። በ67ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ዘውገ የሰበታን መሪነት አስተማማኝ ሲያደርግ በድሉ በመጠቀም 2003 ከፕሪምየር ሊጉ የወረደው ሰበታ ከተማ ወደ ሊጉ ለመመለስ መንገዱን ማመቻቸት ችሏል።

ለገጣፎ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ ከ አውስኮድ ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በስምንተኛው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ ተማም ለለገጣፎ መሪ ማድረግ ቢችልም በ88ኛው ደቂቃ ሚካኤል ጆርጅ ዘንድሮ እየተቸገረ የሚገኘው አውስኮድን የታደገች ጎል አስቆጥሯል።

ደሴ ላይ በጥሩ የውጤት ጎዳና ላይ የሚገኘው ደሴ ከተማ ጎረቤቱ ወልዲያን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። የቀድሞ ክለቡ ላይ በ4ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው በድሩ ኑር ሁሴን የብቸኛዋ ጎል ባለቤት ነው።

ኒያላ ሜዳ ላይ አቃቂ ቃሊቲ ሌላኛውን የመዲናው ክለብ ፌዴራል ፖሊስን ገጥሞ 3-1 አሸንፏል። ሳምሶም ተሾመ በ10ኛው ደቂቃ፣ ጉልላት ተሾመ በ75ኛው ደቂቃ እንዲሁም ፈይሲል መሐመድ በ85ኛው ደቂቃ ላይ የአቃቂ ቃሊቲን ጎሎች ሲያስቆጥሩ ለፌዴራል ፖሊስ ኃይለየሱስ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል። ከጫውታው በኋላ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል አሰልጣኝ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በዳኝነቱ ላይ በነበራቸው ቅሬታ ክስ ማስመዝገባቸውን ነግረውናል።

ወደ ቡራዩ ያመራው ወሎ ኮምቦልቻ 1-0 አሸንፏል። ከደሴ ከተማ በግማሽ ዓመት ላይ ወሎ ኮምቦልቻን የተቀላቀለው አትክልት ንጉሴ የብቸኛዋ ጎል ባለቤት ነው።

ቅዳሜ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ዱከም ላይ አክሱም ከተማን ያስተናገደው ገላን ከተማ 1-0 አሸንፏል። የመጀመርያው አጋማሽ የሁለቱም ጨዋታ በእንቅስቃሴ ጥሩ የነበረ ቢሆንም የጎል ዕድሎች እምብዛም ሲፈጠሩ አልታየም። ለግብ ክልላቸው በእጅጉ ቀረረበው ሲከላከሉ የነበሩት አክሱሞች ሙከራ በማድረግ የተሻሉ ነበሩ፤ በ25ኛው ደቂቃ ሙሉጌታ ረጋሳ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ልዑልሰገድ አስፋው ሞክሮ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። እንግዶቹ ከዚህ በተጨማሪም በ33ኛው እና በ45 ኛው ደቂቃ ላይ በልዑልሰገድ አስፋው እና በድሉ መርዕድ ወደ ግብ አክርረው በመምታት ሙከራን አድርገዋል።

በርካታ የሜዳ ላይ ጥፋቶች እንዲሁም ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ገላኖች ተሻሽለው በመቅረብ የጠራ የግብ እድል መፍጠር ችለዋል። በ49ኛው ደቂቃ አንተነህ ደርቤ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ51ኛው ደቂቃ እሸቱ ጌታሁን ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች። በ60ኛው ደቂቃ ደግሞ ከማዕዘን ምት የተመለሰውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሚኪያስ ዓለማየሁ በአግባቡ በመቆጣጠር ወደግብ አክርሮ መትቶ ገላንን አሸናፊ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።

ከጎሉ በኋላ በአክሱሞች በኩል በ72ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን እድል ልዑል ሰገድ አስፋው ቢሞክረውም የግቡን ቀኝ አግዳሚ ታካ ስትወጣበት በ78 ደቂቃ ላይ ፍፁም ክፍሌ ከመስመሩ ላይ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ያደነበት የግብ ሙከራ በጨዋታው የታየ ተጠቃሽ ድንቅ የግብ ሙከራ ነበር። በገላን በኩል ደግሞ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሚካኤል ደምሴ በመልሱ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ ወደግብነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ የአክሱም ተከላካይ ደርሶ ያዳነበት ተጠቃሽ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡