ከፍተኛ ሊግ | በተስተካካይ ጨዋታዎች ለገጣፎ ነጥቡን ከሰበታ ጋር ሲያስተካከል አውስኮድም አሸንፏል

በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረጉ የቆዩ የምድብ ሀ ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ሲደረጉ ለገጣፎ እና አውስኮድ አሸናፊ ሆነዋል።

ለገጣፎ ላይ በ14ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ደሴ ከተማን የገጠመው ለገጣፎ ለገዳዲ 4-1 አሸንፏል። በርካታ የጎል ሙከራ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ እንግዶቹ ደሴዎች በ1ኛው ደቂቃ በድሩ ኑርሁሴን በግንባሩ በመግጨት ባደረገው የግብ ሙከራ ቀዳሚውን አጋጣሚ ሲፈጥሩ ከሁለት ደቂቃ በኋላ የለገጣፎው ሐብታሙ ፍቃዱ ከቀኝ መስመር እየገፋ በመግባት የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ መትቶ ወጥቶበታል። በአጭር ቅብብል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ የቻሉት ለገጣፎች በሳዲቅ፣ ሐብታሙ እና ሱራፌል አየለ በተደጋጋሚ ጥሩ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ የዋሉ ሲሆን በ31ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። ሐብታሙ ያሻገረውን ኳስ አንዋር አብዱልጀበል በግንባሩ በመግጨት ነበር ለገጣፎን ቀዳሚ ያደረገው።

በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዋቹ ለገጣፎዎች የአየሩን ነፋሻማት በመጠቀም ከርቀት በሚመቷቸው ሙከራዎች ኳስ የደሴን ግብ ጠባቂ የፈተኑ ሲሆን በ46ኛው ደቂቃ ላይ በሱፍቃድ ነጋሽ ከርቀት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲመልሰው ያገኘው ሐብታሙ ፍቃዱ በቀላሉ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል። ከ9 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሳዲቅ ተማም ከረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ በመቆጣጠር ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ አክርሮ ከመረብ በማሳረፍ የለገጣፎን መሪነት ወደ ሦርት አስፍቷል።

እንግዶቹ ደሴዎች ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ጫና በመፍጠር በ64ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ አላዛር ዝናቡ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ቢችሉም በአንድ ደቂቃ ልዩነት መክብብ ወልዴ በግምት 30 ሜትር ርቀት ላይ አክርሮ በመምታት ባስቆጠረው ጎል መልሶ በማስፋት ጨዋታው በለገጣፎ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለገጣፎ ለገዳዲ በድሉ ታግዞ ከመሪው ሰበታ ከተማ ጋር በእኩል 31 ነጥብ በጎል ልዩነት ተበልጦ በሁለተኛ ላይ መቀመጥ ችሏል። (በአምሀ ተስፋዬ)

በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም የተከናወነው የአውስኮድ እና ፌዴራል ፖሊስ የ12ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጨዋታው ገና ከጅማሮው የግብ ሙከራዎችን ያስተናገደ ቢሆንም ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ግን መቀዛቀዝ ታይቶበታል። በሁለተኛው ደቂቃ ባለሜዳዎቹ አውስኮዶች ሳሙኤል አባተ ከቅጣት የተሻገረውን ኳስ በግምባሩ በሞከረው አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ሞክረው መክኖባቸዋል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ተጋባዦቹ ፌደራል ፖሊሶች ደግሞ በተራቸው ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ ሰይፈ ዘኪር መቶት ተጨርፎ በተመለሰ ኳስ ጥሩ አጋጣሚ ያገኘው አብነት ደምሴ አክርሮ በመምታት ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሮ ወጥቶበታል። በሁለተኛ ዙር መጠነኛ መሻሻል የታየባቸው አውስኮዶች ተረጋግተው በመጫወት የግብ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በተቃራኒው ፌደራል ፖሊሶች ደግሞ በግዙፎቹ የመሃል ሜዳ ተጨዋቾቻቸው አማካኝነት ረጃጅም ኳሶች በመጣል ወደ ግብ ለመቅረብ ጥረት አድርገዋል። በ16ኛው ደቂቃ የፌደራል ፖሊስ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ኳስ ያገኘው ሰዒድ ሰጠኝ ከርቀት አክርሮ በመምታት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ጫና ከማድረጋቸው የተነሳ ኳስ ያገኙት ፖሊሶች የፊት መስመር አጥቂያቸው ሰይፈ በሞከረው ሙከራ መሪ ለመሆን ጥረዋል። በደቂቃ ልዩነት የመጀመሪያውን እድል የፈጠረው ሰይፈ ከቀኝ መስመር መነሻነቱን ባደረገ ኳስ ሌላ ሙከራ አድርጎ ለጥቂት ወጥቶበታል። በአንፃራዊነት በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻለ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አውስኮዶች በ31ኛው ደቂቃ ሐቁምንይሁን ገዛኸኝ በሰነዘረው ጥቃት ወደ መሪነት ሊሸጋገሩ ተቃርበው ነበረ። ከዚህች ሙከራ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች የጠራ የግብ ማግባት እድል ሳይፈጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ በነበሩት የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች የተሟሟቀው ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች በሚሰነዝሯቸው ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎች ግብ ለማስተናገድ ተቃርቦ ነበር። በ50ኛው ደቂቃ ፌደራል ፖሊሶች አብነት ለሰይፈ አቀብሎ ሰይፈ ባመከነው ኳስ ጥሩ ሙከራ ሲያደርጉ ባለሜዳዎቹ አውስኮዶች ደግሞ በ51ኛው ደቂቃ በኃይሉ ወልዴ አክርሮ በመታው እና በ53ኛው ደቂቃ ሰዒድ ሰጠኝ በፈጠረው ጥሩ እድሎች ወደ ግብ ቀርበዋል። በተለይ በ53ኛው ደቂቃ ሠይድ የፈጠረው ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ እጅጉን ለግብነት የተቃረበ እድል ነበር።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ኳስን ተቆጣጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት አውስኮዶች በ58ኛው ደቂቃ ባገኙት የፍፁም ቅጣት ምት መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሐቁምንይሁን ገዛኸኝ አስቆጥሮ መሪ ሆነዋል። ከግቡ መቆጠር በፊት ቀጥተኛ አጨዋወትን ለመከተል ሲጥሩ የነበሩት ፖሊሶች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ግን በአንፃራዊነት አጥቅተው ለመጫወት ሞክረዋል። በዚህም በ75ኛው ደቂቃ ጥሩ እድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርቷል። በዚህ ደቂቃ ከግብ ክልላቸው ጀምሮ ኳስ መስርተው የመጡት ፌደራል ፖሊሶች የቡድናቸው አምበል ታዬ አስማረ በሞከረው ጥሩ ኳስ አቻ ለመሆን ጥረዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂዎች ላይም ጫና ማሰደራቸውን ቢቀጥሉም ፍሬ ማፍራት ሳይችሉ ተሸንፈው ወጥተዋል። (በሚካኤል ለገሰ)

በሌሎች ጨዋታ ኮምቦልቻ ላይ ወሎ ኮምበልቻ ከ ገላን ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ገላኖች በ25 ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት መንግስቱ ባባስቆጠረው ጎል ረጅም ደቂቃዎች ቢመሩም በ75ኛው ተመስገን ተስፋዬ ኮምቦልቻን አቻ አድርጓል። ወልድያ ላይ ወልዲያ ከተማ ከቡራዩ ከተማ 1-1 የተጠናቀቀው ጨዋታም ሌላው የዛሬ መርሐ ግብር ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡