የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ


በፕሪምየር ሊጉ 21ኛ ሳምንት አሰላ ላይ ተደርጎ ያለ ጎል ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” የሁለተኛ አጋማሽ ቅያሪዎቻችን ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት እንደመጣን ማሳያ ነው” አዲሴ ካሴ (ሀዋሳ ከተማ)

ስለ አቀራረባቸው

እንዳያችሁት ንፋሱ የሁለታችንን እንቅስቃሴ የረበሸ ይመስለኛል። ኳሶቻችን በሙሉ ረጃጅሞች ነበሩ። ኳሱን ይዘን መጫወት አልቻልንም። ኳስ ይዘን መጫወት ያልፈለግነው እንዲህ ያለ ንፋስ ያለው ሜዳ ያጋጥመናል ብለን ስላልጠበቅን ነው። አጭር ኳስ እንጫወት ብንል ኳሶቻችንን እየነጠቁ ወድያወኑ ሊያጠቁን ስለሚችሉ ያለን አማራጭ ረጃጅም ኳስ መጠቀም ሆኗል።

በዛሬው ጨዋታ አቻ ፈልጋቹ ነው የመጣችሁት?

በፍፁም፤ ሦስት ነጥብ ነው ፈልገን የመጣነው። ምክንያቱም አቻ ምንም አይጠቅመንም። ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ለኛም ለነርሱም ውጤቱ አስፈላጊ ነበር። ከእረፍት መልስ ቅያሪ ያደረግነው አጥቂዎችን ያስገባነው ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት እንደመጣን ማሳያ ነው።

ከሜዳ ውጭ መጫወታቹ ዕድሉን አሳጥቶናል ትላላችሁ ?

ይህን ጨዋታ እሁድ ሀዋሳ ላይ አግኝተነው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ነበር። በሁሉም ረገድ ተዘጋጅተን ነበር። እንደዚህ ዓይነት ሜዳ ስንጫወት እንደሚከብደን እናውቅ ነበር። ታፈሰ ሰለሞንን ያሳረፍነው በሜዳው አለመቸት ነው። ሜዳችን ላይ ተጫውተን የነበረ ቢሆንና ታፈሰን አስገብተን ብንጫወት እርግጠኛ ነኝ የተሻለ ነገር ሰርተን እንወጣ ነበር።

“ጨዋታውን አስቸጋሪ ያደረገው ከባዱ ንፋስ እና የሜዳው አለመመቸት ነው” ስቴዋርት ሀል (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው አስቸጋሪ ነው። አስቸጋሪ ያደረገው ከባዱ ንፋስ እና የሜዳው አለመመቸት ነው። በዚህም አየር ላይ ኳስ ለመጠቀብ ብናስብም ንፋሱ የሚረብሸን ሆኗል። ይህም ባሰብነው መልኩ እንድንቀሳቀስ አላደረግንም። ንፋሱን እየተላመዱ ሲመጡ ግን በተለይ ከእረፍት መልስ የተጫዋቾቼ የመጫወት ፍላጎት እና ወደ ፊት ለማጥቃት በመቅረብ ጥሩ ነበሩ። ጎል መሆን የሚችሉ አምስት ኳሶችን አሜ ፣ አቡበከር እና ሪቻርድ ሳይጠቀሙበት ቀርተናል። እንደምታቁት ሳላዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ በጉዳት አለመኖር የሚፈጥረው ክፍተት አለ።

ከዋንጫው ፉክክር ከወዲሁ ወጥታችኃል ማለት ይቻላል?

እግርኳስ ነው፤ ውድድሩ ገና ነው። በሜዳችን ከዚህ በኋላ አምስት ጨዋታዎች በተከታታይ እንጫወታለን። ይህ ማለት እነዚህን ጨዋታዎች ብናሸንፍ አስራ አምስት ነጥብ ማለት ነው። ወደ መሪነት ተመልሰን የዋንጫ ተፎካካሪ ሆነን ከሜዳችን ውጭ ያሉትን ጨዋታ እየጠበቅን እስከ መጨረሻው እንሄዳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡