የአሰልጣኞች አስተያየት | ደቡብ ፖሊስ 0-0 ወላይታ ድቻ

ከ21ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መካከል የቦታ ለውጥ ተደርጎበት አዲስ አበባ ላይ በዝግ ስታድየም የተከናወነው የደቡብ ፖሊስ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ያለግብ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ ይህን ብለዋል።

”ዕድሎችን ካልተጠቀምን ወደ ጎል መድረሱ ብቻ ጥቅም የለውም” አሸናፊ በቀለ (ወላይታ ድቻ)

ስለ ጨዋታው 

ጨዋታውን የማሸነፍ ፍላጎት ነበረን፤ ቢሆንም አልተሳካልንም። ያገኝናቸውን የግብ አጋጣሚዎች አለመጠቀም ነው፤ እንደተመለከታችሁት ብዙ የግብ እድሎችን አምክነናል። በተደጋጋሚ ወደግብ ደርሰናል። ቢሆንም ግን እድሎችን ካልተጠቀምን መድረሱ ብቻ ጥቅም የለውም። ስለዚህ ማሸነፍ አልቻልነም። እርግጠኛ ነኝ የነሱም ፍላጎት ማሸነፍ ነበር። ምክንያት ያለንበት ቀጠና ለሁለታችንም ጥሩ አይደለም። ስለዚህ የዛሬውን ውጤት እንፈልገው ነበር።

በዝግ ስታድየም ስለመጫወታቸው

የእግርኳስ ውበት ተመልካች ነው። የተጫዋቾችን የመጫወት ፍላጎት እና መነሳሳት ይጨምራል፤ ውበትም ይኖረዋል። የስፖርታዊ ጨዋነት
ጉዳይ የሁላችንም ነው። ስፖርቱ ውስጥ እስካለን ድረስ ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ ነው። ስፖርቱ ህዝብን የሚያዋድድ የሚያፋቅር ነው መሆን ያለበት። ስፖርቱ ውስጥ ያለን ሰዎች ትኩረት ሰጥተን ልንሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። መስመሩን እየሳተ ስለሆነ ደስታ የሚሰጥ ነገር የለም። የሰው ልጅ ተደብድቦ መሄድ የለበትም ብዬ ነው የማስበው።

” የምንፈልገውን ነገር አላገኘንም” ገብረክርስቶስ ቢራራ (ደቡብ ፖሊስ)

ስለ ጨዋታው

አጠቃላይ ጨዋታውን ስናየው ካለፉት ጨዋታዎች አንፃር የዛሬው ወረድ ያለ ነው። ምክንያቱም ከፍተኛ ቦታ ላይ መጥተን ነው የተጫወትነው። ያ ደግሞ እንደዚህ አይነት ችግር እንዲገጥምህ ያደርግሀል። ተጫዋቾችም የድካም ስሜት ይታይባቸው ነበር። የምንፈልገውን ነገር አላገኝንም። በሜዳችን ተጫውተን ቢሆን ሁለቱን ነጥብ ማግኝት እንችል ነበር።

በዝግ ስታድየም ስለመጫወት

አሁን እኮ ስታየው ልምምድ ነው የሚመስለው፤ እግር ኳስ ያለ ደጋፊ ባዶ ነው። እግር ኳሱ ሁልጊዜ ድጋፍ ይፈልጋል። ደጋፊዎች መኖር አለባቸው። እኛ በመሰረቱ ደጋፊ የለንም። ግን ያለ ደጋፊም ቢሆን በትክክለኛ በሜዳችን ብንጫወት ጥሩ ነው። ደጋፊው የሚዝናናበት ስፖርት ማጣት የለበትም፤ ያ ነገርም ቢኖር አቻችለን ነው ማድረግ ያለብን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡