U-20 ምድብ ሀ | ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ሲረከብ ቡና፣ መከላከያ እና ወላይታ ድቻ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀመሩ በምድብ ሀ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ከሜዳቸው ውጪ ድል አስመዝግበዋል። ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻም ድል ያስመዘገቡ ቡድኖች ሆነዋል።

4:00 ላይ በአካዳሚ ሜዳ ኢትዮጵያ ቡና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን 3-0 አሸንፏል። ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረ ጨዋታ በጎል ሙከራ ያልታጀበ ሲሆን በሂደት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ ወደ ጎል በመቅረም የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም የአካዳሚው ግብ ጠባቂ ዳዊት ኃይሉ ንቃት ጎል መሆን የሚችሉ እድሎች መክነውባቸዋል። ኳስ ይዘው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመስመር አጥቂያቸው በየነ ባንጃ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ግብ ጠባቂው ዳዊት አድኖባቸዋል። የአካዳሚ ተከላካዮችን ክፍተት በመጠቀም የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ በኃይሉ ተስፋዬ ነፃ ኳስ አግኝቶ በድጋሚ የአካዳሚው ግብጠባቂ ዳዊት አድኖበታል። በሂደት መሻሻል ያሳያሉ ቢባልም አማካዮ ሰለሞን ያለው በግሉ ከሚያደርገው መልካም እንቅስቃሴ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልለ በመድረስ አካዳሚዎች የፈጠሩት አደጋ አልነበረም።

በግብጠባቂው ዳዊት ጥረት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጎል ሳያስቆጥሩ ወደ እረፍት ያምሩ እንጂ በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ጎልነት በመቀየር ስኬታማ ነበሩ። ከመሐል ሜዳ አጋማሽ የተጣለለትን በኃይሉ ተስፋዬ ኳሱን ከተከላካዮች በሰውነቱ ሸፍኖ በመግባት ባስቆጠረው ጎል ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ፊት መስመራቸው ላይ ቅያሪዎችን ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን ቀጥለው ኪቲካ ጆማ ከቀኝ መስመር ቆርጦ በመግባት አስራ ስድስት ከሃምሳ ጠረዝ ላይ አክርሮ በመምታት እጅግ ግሩም ጎል ለኢትዮጵያ ቡና አስቆጥሯል።

አካዳሚዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሂደት የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሰለሞን ያለው ወደ ጎል የሞከረውን የቡናው ግብጠባቂ ዳዊት ባህሩ ወደ ውጭ ያወጣበት አካዳሚዎች የፈጠሩት ተጠቃሽ የግብ ዕድል ነው። ከአንደኛው ዙር በአንፃራዊነት ተሻሽለው የቀረቡት ቡናዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለው ያገኙትን ቅጣት ምት አማኑኤል ኤርቦ ግብጠባቂው ባጠበበበት ቦታ በጥሩ ሁኔታ መሬት ለመሬት መትቶ ያስቆጠራት የጨዋታው ማሳረጊያ ሦስተኛ ጎል በመሆን ጨዋታውን ኢትዮጵያ ቡና በ3-0 አሸናፊነት አጠናቋል። (በዳንኤል መስፍን)

መከላከያን በሜዳው ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 3-1 ተሸንፎ መሪነቱን ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስረክቧል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ወስደው የነበሩት ሀዋሳዎች ቢሆኑም መከላከያዎች በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መሰንዘር ችለዋል። በ2ኛው ደቂቃ የመከላከያ ተከላካዮች
ወደ ኋላ ለግብ ጠባቂው ሲሰጡ ግብ ጠባቂው ከእግሩ አምልጣ በራሳቸው ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በመከላከያዎች በኩል የመሀመድ አበራ እና ሰለሞን ሙላው እንቅስቃሴ ለሀዋሳ ተከላካዮች ፈታኝ ነበሩ። በተለይ ከቅጣት ምት ሰለሞን ሙላው በቀጥታ አክርሮ መትቶ በእለቱ ድንቅ የነበረው የሀዋሳ ግብ ጠባቂ ደሳለኝ ንጉሴ እንደምንም ሲይዝበት ወደ መጨረሻ የእረፍት መውጫ ደቂቃዎች ላይ አቤል ነጋሽ ከአማካይ ክፍሉ ያገኘውን ዕድል በቀላሉ በግብ ጠባቂው ይዞበታል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የመከላከያ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውጤታማ የሆነበት ሲሆን ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች በተከላካዮቻቸው ስህተት በሚገኙ ኳሶች በመከላከያ አጥቂዎች እጅጉን ተፈትነዋል፡፡ 55ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ገዛኸኝ በግል ጥረቱ ወደ ሳጥን ውስጥ እየገፋ ገብቶ ያቀበለውን ምንተስኖት እንድሪያስ ወደ ግብነት ለውጦ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ መከላከያዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ፍፁም የሆነ ብልጫን ጭምር በመውሰድ መጫወት የቻሉ ሲሆን 75ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በግራ አቅጣጫ መሳፍንት ጳውሎስ ማራኪ ግብ በማስቆጠር መከላከያን አቻ አድርጓል።

79ኛው ደቂቃ በግሩም ቅብብል ከዊሊያም ሰለሞን የተሻገረውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ በመንቀሳቀስ አድናቆት የተቸረው መሐመድ አበራ ግብ በማስቆጠር መከላከያን መሪ አድርጓል። መሐመድ በ88ኛው ደቂቃ ላይም ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ሆኖም ይህቺ ግብ ስትቆጠር አስቀድሞ የሀዋሳ ተከላካይ ላይ ጥፋት ተሰርቷል፤ ግቧ አግባብ አደለችም በሚል ሀዋሳዎች በዋናው እና ረዳት ዳኛው ላይ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በመከላከያ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ (በቴዎድሮስ ታከለ)

ወደ አምቦ ያመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምቦ ጎል ጋር ያደረገውን ጨዋታ 6-3 አሸንፏል። ድሉን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ከሀዋሳ ከተማ መረከብ ችሏል።

በሌሎች ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ በሜዳው ጥሩነሽ ዲባባን 4-0 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡