ለሦስት ወራት ከሜዳ የራቀው ሚኪያስ መኮንን ዳግመኛ ጉዳት አስተናገደ

ያለፉትን ሦስት ወራት በጉዳት ከሜዳ የራቀውና በቅርቡ ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ ቡናው ሚኪያስ መኮንን ዳግመኛ ጉዳት አስተናገደ።

መቐለ ከተማ ላይ በመጀመርያው ዙር 12ኛ ሳምንት ኢትዮዽያ ቡና ከሜዳው ውጭ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ባደረገው የሊጉ ጨዋታ ላይ ነበር ሚኪያስ መኮንን የብሽሽት ጉዳት ያስተናገደው። ያለፉትን ሦስት ወራትም ከጉዳቱ ለማገገም የተለያዩ ህክምናዎችን እየተከታተለ ቆይቶ ከጉዳቱ በማገገሙ ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ ልምምድ ተመልሶ እንደነበረ ይታወቃል።

ሆኖም ከሦስት ቀናት በፊት ከቡድኑ ጋር ቀለል ያለ ልምምድ እየሰራ ባለበት ወቅት በድጋሚ የብሽሽት ጉዳቱ አገርሽቶበት ልምምድ አቋርጦ ሊወጣ ችሏል። ሚኪያስ መኮንን ከዚህ በኃላ ዳግመኛ ወደ ሜዳ የሚመለስበት ቀን ለጊዜው ያልታወቀ ሲሆን በቅርቡ የሚያደርገው MRI ምርመራ ወደ ሜዳ የሚመለስበትን ቀን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በ2009 ከሐረር ሲቲ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያቀናው ሚኪያስ መኮንን ከአቡበከር ናስር ጋር በመሆን ከተስፋ ቡድን ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ስኬታማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኝ ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡