የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-0 ኢትዮጵያ ቡና

ከ22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መካከል አዳማ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታድየም የተከናወነው የአዳማ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የአዳማ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል አስተያየት ሲሰጡ የኢትዮጵያ ቡናው ገዛኸኝ ከተማ አስተያየት ሳይሰጡ ቀርተዋል።

” ተጫዋቾቼ የደጋፊውን ጭንቀት በደንብ ስለተረዱ ጠንክረን ነበር የሰራነው” አስቻለው ኃይለሚካኤል (አዳማ ከተማ)

ስለ ጨዋታው 

ከሽንፈት መልስ ነው ይህ ጨዋታ ያሸነፍነው። ተከታታይ ሶስት ጨዋታ ነጥብ አጥተናል። ከዛ መልስ ነው ይህ ድል የተመዘገበው። ተጫዋቾቼ የህዝቡን ጭንቀት በደንብ ስለተረዱ ጠንክረን ነበር የሰራነው። ከቴክኒኩ በተጨማሪ የሥነ-ልቡና ስራ ሰርተናል። ጨዋታው እንዳያችሁት ጥንቃቄ ያለው ነበር። ፊት መስመር ላይ ከሌላው ጊዜ የተሻለ ነበርን። ጥሩ ጨዋታ አሳይተናል፤ ብልጫም ወስደናል። ተጋጣሚያችንም ጥሩ ነበር።

ስለ ተጫዋች ቅያሪ እና የጉዳት ተፅዕኖ

የተጫዋች ለውጥ በልምምድ ሜዳ ላይ በምትሰራው ስራ ላይ የምታየውን ነው። ጨዋታ የሚቀይር ማነው ብለህ ታስተውላለህ። አጋጣሚ ሆኖ የአዳማ የፊት መስመር በጉዳት በጣም ሳስቷል። ከጉዳት የተመለሰው ቡልቻ ትልቅ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ባጠቃላይ የተጫዋች ጉዳት ውጤታችን ላይ ተፅዕኖ አድርጓል።

ደረጃ ስለማሻሻል

አዳማ ቡድኑ አሁን ካለው የተሻለ ደረጃ ይዞ ይጨርሳል፤ በዚህ እርግጠኛ ነን። በቡድን እንቅስቃሴ በኩል ትናንሽ ስህተቶች አሉ። በነዚህ አጋጣሚ ግብ ይቆጠራል፤ እኛም ብዙ እንስታለን። አዳማ አሁን ያለበት ደረጃ አይመጥነውም። ብዙ ቡድን ጋር ስንጫወት ጥሩ ነበርን። አሁን ካለንበት ደረጃ ከፍ በማለት እናጠናቅቃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡