የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-0 ድሬዳዋ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ድሬድዋ ከተማን አስተናግዶ 2 – 0 አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” ደጋፊው ደከም ስንልም ሊደግፉን ይገባል ” ውበቱ አባተ (ፋሲል ከነማ)

ስለ ጨዋታው

ተጋጣሚያችን ድሬዳዋ ሶስት ተከታታይ ጨዋታ አሸንፎ ነበር ያገኘነው። ጥሩ መነሳሳት ላይ ሆኖ ነው የገጠመን። በተቃራኒው የኛን ደግሞ ስንመለከት ትንሽ ከተመልካች ጋር በተያያዘ ትንሽ ጫና ውስጥ ተጫዋቾች እየገቡ ነው። ከእረፍት በፊት በእንቅስቃሴ ጥሩ ነበርን። ከእረፍት በኋላ ግን ድሬድዋ የተሻለ ነበር። ተጭነው እየተጫወቱ ነበር ግን አንዳ አንድ ጊዜ ጨዋታ መቆጣጠር እና ኳስ መቆጣጠር ይለያያል። ጨዋታ በመቆጣጠር ደረጃ እኛ የተሻልን ነበርን። እነሱ ኳስ መቆጣጠር ቢችሉም ዞሮ ዞሮ ግን ሜዳችን ላይ ያለውን ፍርሀት ለማራገፍ ሞክረናል። ካያችሁት ደጋፊውንም ወደመጨረሻ ነው መጨፈር የጀመረው፤ አንዳንዴ ደከም ስንልም ሊደግፉን ይገባል። በተለይ ደከም ስንል የነሱን ድጋፍ እንፈልጋለን። ዞሮ ዞሮ ግን ጥሩ ጨዋታ ነበር።

ስለ ዋንጫ ፉክክር

ከእንግዲህ ጨዋታዎች እያነሱ ነው የሚሄዱት። ስለዚህ እየቆጠርን ነው የምንሄደው። ያገኝነውን ነጥብ እየሰበሰብን ነው መሄድ ያለብን። እሱን ካደረግን የዋንጫ ፉክክር ውስጥ እስከ መጨረሻው እንቆያለን። በእኛ በኩል እስከ መጨረሻው ነጥብ ሳንጥል መሄድ ነው የሚጠበቅብን። ያው የነሱም መጣል ይጠበቃል ። በስነልቦና ደረጃ ተጫዋቾቸ ትልቅ መነሳሳት ላይ ናቸው። ደጋፊው እንደሚታወቀው ፍላጎቱ ትልቅ ነው። ያን የማሳካት አቅም እንዳለን ይታየኛል።

” የትኩረት ማነስ የዛሬውን ጨዋታ እንድንሸነፍ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ” ስምኦን ዓባይ (ድሬዳዋ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው እንደተመለከታችሁት በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ላይ የሰራነው ስህተት ዋጋ ያስከፍሉንን ነገሮች ሰርተን ልንሸነፍ ችለናል። ጨዋታው 30 ደቂቃዎች እስኪያስቆጥር ድረስ ተጫዋቾቸን በአዕምሮ ያወረዳቸው ያመስለኛል። ከመጀመሪያው ጥሩ አልነበሩም። ከዛ በኋለ በነበሩ ደቂቃዎች ጥሩ ነበርን። በመጀመሪያው አጋማሽ 10 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው ሁለት ግብ የተቆጠረብን። ስለዚህ የትኩረት ማነስ የዛሬውን ጨዋታ እንድንሸነፍ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ብዬ አምናለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡