የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

የቀን ለውጥ

በምድብ ሐ በሠንጠረዡ አናት ላይ የሚገኙት ክለቦች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ትኩረት ስበዋል። እሁድ መርሐ ግብር ወጥቶላቸው የነበሩትና ካፋ ቡና ከምድቡ መሪ ሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም ሻሸመኔ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ወደ ሰኞ 4:00 ተሸጋግረዋል።

የይግባኝ ሰሚ ውሳኔ እና ቅሬታ

ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና ከሻሸመኔ ባደረጉት ጨዋታ ሻሸመኔዎች ጨዋታውን አቋርጠው በመውጣታቸው ካፋ ቡና ፎርፌ (3 ነጥብ እና 3 ጎል) እንዲያገኝ፤ በጨዋታው ለተፈፀመው የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ደግሞ የሜዳው ሁለት ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጭ እንዲጫወት በዲሲፕሊን ኮሚቴ ተወስኖ እንደነበር ይታወሳል። ውሳኔው በይግባኝ ሲታይ ቆይቶ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ውሳኔ ተሽሮ ጨዋታው በገለልተኛ እና ዝግ ስታድየም እንዲደገም ሲወሰን ካፋ ቡና የተቀጣው ሁለት ጨዋታ ደግሞ ወደ አንድ ዝቅ ተደርጎ ፌዴሬሽኑ በሚወስነው ሜዳ እንዲያካሂድ ተወስኖበታል። ይህን ተከትሎም ከሀዲያ ሆሳዕና የሚደርገው የዚህ ሳምንት ጨዋታ በወልቂጤ ሜዳ እንዲከናወን ውሳኔ ተላልፏል።

ይህን ውሳኔ ተከትሎ ካፋ ቡናዎች ለሶከር ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። የክለቡ ስራ ፕሬዝዳንት አቶ ሽፈራው ” በውሳኔው በጣም ነው ያዘንነው። ዲስፕሊን ኮሜቴ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ 21 ቀናት ቆይቶ ይግባኝ ሰሚው የዲስፕሊን ኮሚቴን ውሳኔ በመሻር፣ የዳኛውን ውሳኔ ወደ ጎን በማድረግ ፎርፌ እና ሶስት ንፁህ ጎሎችን ሰርዟል፤ እንዲሁም የሜዳ ቅጣቱን አፀንቶታል። በውሳኔው ቅር ካሰኘን አንደኛው እና ዋናው ነገር ዘግይቱ ውሳኔ መድረሱ ነው። ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታችን ቀድሞ ነበር መነገር ያለበት። የሜዳ ምርጫ እድል ለኛ ሊሰጥ ይገባ ነበር። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ፤ በተጨማሪም የዕለቱ ዳኛ ፍፁም ቅጣት ምት እንዲሆን የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ሻሸመኔዎች ጨዋታውን አቋርጠው በመውጣታቸው የተወሰነውን ቅጣት በመሻር ጨዋታው እንዲደገም ውሳኔ ማስተላለፉ በራሱ ፍትሀዊነቱን ያልጠበቀ ነው። ዛሬ በአካል በመሄድ ፌዴሬሽኑን በአካል ብናናግርም ጨዋታውን ሰኞ 4:00 ወይም እሁድ 9:00 ሰዓት ማከናወን እንደምንችል ገልፀውልናል። የቴክኒክ ክስን ይግባኝ ሰሚ ኮሜቴ የዳኛን ውሳኔ መቀየር የሚችልበት ምንም አይነት አግባብነት የለውም። በአጠቃላይ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያስተላለፈው ውሳኔ ፍትሀዊ ያልሆነ እና ቡድናችንን በአቅምም ሆነ በዝግጅነት የሚያዳክም እንደሆነ መታወቅ መቻል አለበት።” ብለዋል።

ኢትዮጵያ መድን

በ2011 ውድድር ዓመት ኢትዮጵያ መድንን የተቀላቀሉት አሰልጣኞች በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የገቡትን ቃል መተግበር አልቻሉም በሚል ለአሰልጣኝ ስብስቡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ታውቋል። ዋና አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ እና ረዳቶቹ ከማስጠንቀቂያው በፊት በሁለት ጨዋታዎች ውጤት ላይ ከክለቡ ጋር ምክክር ያደረጉ ሲሆን በተጫዋቾቻቸው የሥነ ምግባር ጉዳይ ላይም ውይይት አድርገው እንደነበር ታውቋል።

ኢኮስኮ

በዚህ ሳምንት በምድብ ለ የሚጠበቀው የኢኮስኮ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ከወዲሁ ትኩረት ስቧል። ኢኮስኮዎች የሜዳ ጨዋታቸውን ለማድረግ ያስመዘገቡት መድን ሜዳን ከመሆኑ አንፃር ይህም ጨዋታ በዚሁ ሜዳ የሚከናወን በመሆኑ የሜዳ ለውጥ እንዲደረግ ኢኮስኮዎች ለፌዴሬሽን ጥያቄ አቅርበው አዎንታዊ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። ” የዛሬ አስራ አምስት ቀን ተጋጣሚያችን ወልቂጤ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት አወዳዳሪው አካል አምኖበት ጨዋታውን ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ለውጦታል። ያኔ እኛ ተቃውሞ አላሰማንም። ሆኖም ዛሬ ላይ የተጋጣሚያችን ሜዳ እንደመሆኑ መጠን ወጥተን እንጫወት ዘንድ እድል ሊሰጠን ይገባ ነበር። ከዚህ ቀደም ድሬዳዋ ስታዲየም ምንም ጨዋታ ሳይኖረው መጫወት ሲገባን በሳቢያን ሜዳ እንድንጫወት ተገደናል። ይህም ጨዋታ የሚደረገው የተጋጣሚያችን ሜዳ ላይ እንደመሆኑ መጠን ወጥተን እንጫወት ዘንድ እድል ሊሰጠን ይገባ ነበር። ” ሲሉ የክለቡ አመራሮች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የከፍተኛ ሊግ ኮሜቴ አባል ሻምበል ሀለፎም ምሩፅ ከሶከር ኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ስለ ኢኮስኮ የሜዳ ጥያቄ ይህን ብለዋል። ” የአዲስ አበባ ስታዲየም እሁድ ዕለት በመያዙ፤ ሁሉም ጨዋታ ደግሞ በእኩል ቀን እና ሰዓት መጀመር ስላለበት ነው ይህን ያደረግነው። ከዚህ በፊት የሜዳ ለውጥ ያደረግነው የፀጥታ ችግርን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ” 

አርባምንጭ ከተማ

በምድር ሐ ተመድቦ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ለፌዴሪሽኑ ቅሬታ ያስገባ ሲሆን የቡድኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ ንጉሴ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ” ሁሉም ቡድን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ነው ነጥብ ማግኘት ያለበት። ከመቼውም ጊዜ በይበልጥ አወዳዳሪው አካል አሁን ላይ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል። ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ እንዲሁም ላለመውረድ የሚደረገው ትግል ቀላል አይደለም። ቡድናችን ከመሪው ያለው ርቀት በጣም አነስተኛ እንደመሁኑ መጠን የካፋ ውሳኔ አግባብነት የለውም። ውሳኔው የተወሰነው ሚያዚያ 30 ነው። ፌዴሪሽኑ ያሳወቀው ደግሞ ግንቦት 9 ነው። ለምን ይህን ያህል ቀን ቆየ ነው ቅሬታችን። ከጥላቻ ወይም ከሌላ ሀሳብ ሳይሆን ይህ ውሳኔ በቅርብ ርቀት ለምንመለከተው ለኛ ቡድን ተፅዕኖ ስላለው ነው። ቅሬታችን ምላሽ ካላገኘ ውድድሩ ላይ ላንቀጥል እንደምንችል እናስወቃለን። ” ብለዋል።

የ18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር

ምድብ ሀ

እሁድ ግንቦት 11

ሰበታ ከተማ 9:00 ገላን ከተማ
አክሱም ከተማ 9:00 ለገጣፎ ለገዳዲ
ፌዴራል ፖሊስ 9:00 ደሴ ከተማ
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 9:00 ቡራዩ ከተማ
አውስኮድ 9:00 አቃቂ ቃሊቲ
ወሎ ኮምቦልቻ 9:00 ወልዲያ

ምድብ ለ

እሁድ ግንቦት 11

ሀምበሪቾ 9:00 ድሬዳዎ ፖሊስ
ዲላ ከተማ 9:00 ወልቂጤ ከተማ
ነጌሌ አርሴ 9:00 ናሽናል ሲሜንት
ኢኮስኮ 9:00 ኢትዮጵያ መድን
ሀላባ ከተማ 9:00 የካ ክ/ከተማ
ወላይታ ሶዶ 9:00 አዲስ አበባ ከተማ

ምድብ ሐ

እሁድ ግንቦት 11

ነቀምት ከተማ 9:00 ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ
ነጌሌ ቦረና 9:00 ካምባታ ሺንሺቾ
ቤንች ማጂ ቡና 9:00 ስልጤ ወራቤ
ቡታጅራ ከተማ 9:00 ጅማ አባ ቡና

ሰኞ ግንቦት 12

ሻሸመኔ ከተማ 4:00 አርባምንጭ ከተማ
ካፋ ቡና 4:00 ሀዲያ ሆሳዕና (ወልቂጤ)


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡