ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና

የ25ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታን የተመለከተው ዳሰሳችን እንሆ…

ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም 10፡00 ላይ በኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና መካከል የሚደረገው ጨዋታ ለዕንግዶቹ ይበልጥ ትርጉም ያለው ይመስላል። በሁለቱም የሰንጠረዡ ፉክክሮች ውስጥ የማይገኘው ኢትዮጵያ ቡና ከሽረ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ስለመመለስ እያሰበ ያለጫና ወደ ሜዳ ሲገባ መሪው መቐለን በመርታት ወደ መዲናዋ የመጡት ሲዳማዎች የዋንጫ ተስፋቸውን ለማለምለም ሦስቱን ነጥቦች አጥብቀው ይሻሉ።

ባህር ዳርን በሰፊ የግብ ልዩነት ካሸነፈ በኋላ የድል እና የግብ መንገዱን መልሶ ማግኘት ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ ደረጃን ይዞ በመጨረስ አላማ አጥቅቶ የመጫወት ዕቅድ እንደሚኖረው ይገመታል። የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመያዝ እንደሚሞክር የሚጠበቀው ቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ በተጋጣሚው ላይ የበላይ የመሆን ዕድሉ ቢኖረውም ሁለቱን መስመሮች ለመሸፈን ለመስመር ተከላካዮቹ ከፍ ያለ የመከላከል ኃላፊነት መስጠቱ የሚቀር አይመስልም። በእርግጥ የፊት አጥቂው ሁሴን ሻባኒ ብዙ ክፍተት ሸፍኖ መጫወት ሲታሰብ የቡድኑ የመሀል ክፍል ከአጥቂው ወደ ኋላ የተሳበ እንቅስቃሴ ተጨማሪ የቁጥር የበላይነት ከማግኘቱ ባለፈ ከሲዳማ የኋላ መስመር ፊት ለአጥቂ አማካዮቹ የሚሆን ክፍተትም ሊያገኝ ይችላል። በሳምንቱ አጋማሽ ከኮንጓዊው አጥቂ ሱለይማን ሎክዋ ጋር የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና  ወሳኝ ተጫዋቹ አቡበከር ነስሩ ቅጣቱን ባለመጨረሱ ካሉሻ አልሀሰን እና ሚኪያስ መኮንን ደግሞ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው በነገው ጨዋታ የማይጠቀምባቸው ይሆናል። 

መቐለ እና ፋሲልን በመከተል ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በፍልሚያው ለመቀጠል የተፎካካሪዎቹን ውጤት መጠበቅ የግድ ቢለውም ደካማውን የሜዳ ውጪ አቋሙን አስተካክሎ መቅረብ ይጠበቅበታል። መሀል ሜዳ ላይ ሊወሰድበት ከሚችለው ብልጫ እንዲሁም ከመስመር አጥቂዎቹ አደገኛነት አንፃር ሲዳማ ነገ ወደ መልሶ ማጥቃት ያደላ አቀራረብ እንደሚኖረው ይገመታል። በተለይም የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር ወደ መሀል ሜዳ በሚጠጋባቸው አጋጣሚዎች ቡድኑ ከኋላ የሚጥላቸውን ኳሶች በመጠቀም ወደ ሳጥን ውስጥ መግባት ከቻለ አስፈሪነቱ ሊጨምር ይችላል። በጨዋታው ፍቅሩ ወዴሳን ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት መልስ የሚያገኘው ሲዳማ ቡና  አጥቂው መሀመድ ናስርም ከጉዳት ይመለስለታል። ይህም ሀብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግዳይ መነሻቸውን ከሁለቱ ኮሪደሮች በማድረግ በተለመደው ፍጥነታቸው ቡድኑን እንዲረዱ እገዛ ያደርጋል። በሌላ በከል ግን ሚሊዮን ሰለሞን እና መሳይ አያኖ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ታውቋል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሲዳማ ቡና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት 2002 ወዲህ ለ19 ጊዜያት ተገናኝተዋል፡፡ ሲዳማ ቡና 7 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላነቱን ሲወስድ ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ አሸንፏል፡፡ በ6 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሲዳማ ቡና 22 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ  23 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– 14 ጨዋታዎችን በሜዳቸው ያከናወኑት ኢትዮጵያ ቡናዎች ስድስቱን በድል ሲወጡ አምስት የአቻ እና ሦስት የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበዋል።

– ሲዳማ ቡና ከድቻ ጋር በገለልተኛ ሜዳ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ሳይጨምር ከሜዳው ውጪ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያከናወነ ሲሆን ድል የቀናው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በተረፈ ሦስቴ ነጥብ ሲጋራ አምስት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ኢትዮጵያ ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲዳማ ቡናን ደግሞ ከአዳማ እና ሽረ ጨዋታው በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ የሚዳኘው ቢኒያም ወርቅአገኘው ለጨዋታው ተመድቧል። አርቢትሩ በሰባት ጨዋታዎች 34 የማስጠንቀቂያ እና አንድ የቀይ ካርዶችን ሲመዝ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

                                                                        ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-2-3-1)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ቶማስ ስምረቱ – ተካልኝ ደጀኔ
          

አማኑኤል ዮሀንስ – ኄኖክ ካሳሁን

እያሱ ታምሩ – ሳምሶን ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ሁሴን ሻባኒ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ግሩም አሰፋ – ሰንደይ ሙቱኩ

ወንድሜነህ ዓይናለም – ዮሴፍ ዮሃንስ – ዳዊት ተፈራ

ሀብታሙ ገዛኸኝ – መሐመድ ናስር – አዲስ ግደይ           


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡