“ተጫዋቾች አንድ ዓይነት አላማ መያዛቸው ቡድኑ ስኬታማ እንዲሆን ረድቶታል” ጌቱ ኃይለማርያም – ሰበታ ከተማ

የከፍተኛ ሊጉ በተመሳሳይ ቀን ሦስቱንም ክለቦች ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲሸኝ ሰበታ ከተማም ከ8 ዓመታት በኋላ ወደ ዋናው ሊግ ተመልሷል። በየዓመቱ ወጣ ገባ አቋም እያሳየ የነበረው ሰበታ ከተማ ዘንድሮ በወጥ አቋም ለስኬት እንዲበቃ ካስቻሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አምበሉ ጌቱ ኃይለማርያም ነው። ወጣቱ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ከቡድን ስኬቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተካቶ የኦሊምፒክ ማጣርያዎች ላይ በመሳተፍ ጥሩ ጊዜ አሳልፏል። ተጫዋቹ ስለ ሰበታ ውጤታማ ጉዞ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጎ ነበር።

ስኬት

የውድድር ዓመቱ አድካሚ ስለነበር ውጤቱ እንደዚህ ሆኖ ሲያልቅ በጣም ደስ ይላል። ቀደምን ነበር ዝግጅት የጀመርነው። ከመጀመሪያው አንስቶ ሁላችንም ፕሪምየር ሊግ ለመግባት አልመን ነበር ስንሰራ የቆየነው። ቡድኑ ስኬታማ እንዲሁን ከረዱት መካከል አንዱ እና ዋንኛው የቡድኑ ተጫዋቾች አንድ ዓይነት አላማ መያዝ መቻላቸው ነው። የአሰልጣኝ ስብስቡ ተግባራት እና የሚያደርጉት ክትትልም ውጤታማ አድርጎናል። በተጨማሪም አመራሩ በሜዳ ላይ ስራ ጣልቃ አለመግባቱ ሁሉም የስራውን ድርሻ ላይ ብቻ አተኩሩ እንዲጫወት ዕድል ሰጥቶታል።

ያለ ሽንፈት መዝለቅ

በዘንድሮ ውድድር ዓመት እንደ ትልቅ ስኬት የማየው ምንም ጨዋታ ሳንሸነፍ ነው ለዚ ድል የበቃነው። ይህ የተለየ ነገር ሆኖ ሳይሆን በሁሉም ቦታ ላይ የነበረው የቡድኑ ስብስብ ብቃት እና ልምድ ያላቸው መሆናቸው ጠቅሞናል። ከሜዳችን ውጭ ስንጫወት የሚገጥሙን ችግሮች ነበሩ ይህንንም በብቃት አልፈነዋል።

ደጋፊዎች

ደጋፊዎቻችን ትልቁን ቦታ ይይዛሉ። ከመጀመሪያ ጀምሩ እስካሁን ድረስ ድጋፍ እያደረጉልን ነው። ባጠቃላይ ደጋፊውን የክለቡ የበላይ አመራሮች ሜዳ ድረስ በመምጣት እያበረታቱን ነበር አሰልጣኞቻችን ሁሉንም እናመስግናለን። እንኳን ደስ ያለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡