ምስራቅ አፍሪካ | ሴካፋ ካጋሜ የክለቦች ዋንጫ በክፍለ አህጉሪቱ ትላልቅ ክለቦች ትኩረት ተነፍጎታል

ከጁላይ 6 እስከ 21 በሩዋንዳ ኪጋሊ ይደረጋል የተባለው የሴካፋ የክለቦች ዋንጫ በዞኑ ትላልቅ ክለቦች ትኩረት ተነፍጎታል።

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በአወዳዳሪው አካል የተሳትፎ ጥያቄ የቀረበላቸው በሴካፋ አገራት ስር የሚገኙ የሊግ አሸናፊ ክለቦች አብዛኞቹ እስካሁን ድረስ ለአወዳዳሪው አካል የተሳትፎ አፋጣኝ መልስ ያልሰጡ ሲሆን ከሻምፒዮኖቹ መካከል የዩጋንዳው ክለብ ኬሲሲኤ ብቻ በውድድሩ ለመሳተፍ በፍቃደኝነቱ አሳይቷል። ሁለቱ የታንዛንያዎቹ ትላልቅ ቡድኖች ያንጋ አፍሪካና ሲምባ ከሴካፋ የቀረበላቸው ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በውድድሩ እንደማይሳተፉም አሳውቀዋል።

በውድድሩ ፎርማት መሰረት የዞኑ አሸናፊ ቡድኖች ይሁኝታ ያላገኘው አወዳዳሪው አካልም በርከት ያሉ ለመወዳደር ፍቃደኛ የሆኑ ቡድኖች አካቶ ውድድሩ ለማካሄድ ዝግጅቱን ጨርሷል። በዚህም የሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ ፣ የኬንያው ጎር ማህያ ፣ የታንዛንያው አዛም ፣ የዩጋንዳው ኬሲሲኤ ፣ የዛንዚባሩ ኬኤም ኬኤም ፣ የጅቡቲው ኤኤስ ፖርትስ ፣ የሱማልያው ሃገን በተጋባዥነትም የዛምብያው ግሪን ቡፋልስ እና የዲሞራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ ለመሳተፍ በፍቃደኝነታቸው ያሳዩ ቡድኖች ናቸው።

ሴካፋ እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ጅማ አባጅፋር የተወዳደሩ ጥያቄ እንዳላቀረበ ከክለቡ ለማረጋገጥ ችለናል።

በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ስፖንሰርነት የሚካሄደው ውድድሩ ለአሸናፊው ቡድን ሰላሳ ሺህ ዶላር እንዳዘጋጀ ተገልጿል።