ዮርዳኖስ ዓባይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ልምዱን አካፈለ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ዝናቸው ከናኙ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ዮርዳኖስ ዓባይ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ባደረጉለት ግብዣ ዛሬ ብሔራዊ ቡድኑ ባረፈበት ሆቴል በመገኘት ለተጫዋቾች ያለውን ልምድ አካፏሏል።

ለ2020 ቻን ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመልሱን ጨዋታ ከጅቡቲ አቻው ጋር የፊታችን እሁድ ጨዋታውን ለማድረግ በድሬዳዋ ከተማ ዝግጅቱን እያደረገ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በዝግጅታቸው ወቅት ዛሬ ብሔራዊ ቡድኑ በሚገኝበት ሰመረት ሆቴት ለዩርዳኖስ ዓባይ ባደረጉለት ግብዣ ያለውን ልምድ ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች አካፍሏል።

ዮርዳኖስ በንግግሩ ” በመጀመርያ በህይወቴ ከተደሰትኩባቸው ቀናት አንዱ ይሄ ነው። ምክንያቱም በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተከብሬ ይህ መድረክ መመቻቸቱ በጣም አስደስቶኛል። እንዲህ ያለ ጥሪ የመጀመርያዬ ነው። የሚሰማኝን የውስጤን ሀሳብ እንዳካፍል እና እንድናገር በመደረጉ በጣም አመሰግናለው።” ያለው ዮርዳኖስ ” እኛ በነበርንበት የብሔራዊ ቡድን ዘመን ካስመዘገብነው ውጤት እናንተ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አለባችሁ። ለዚህም ሁሌም ጠንክራቹ መስራት ይገባችኋል።” ካለ በኋላ ሰፊ ልምዱን አካፍሏል።

ዮርዳኖስ በመቀጠል በተለይ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ጥያቄ ያቀረቡለት ሲሆን በብሔራዊ ቡድን ፣ በሀገር ውስጥ ክለቦች እና በየመን በነበረህ ቆይታ ለተከታታይ ዓመታት ወጥ በሆነ አቋም ኮከብ ኮል አስቆጣሪ የመሆኑን ሚስጢር አበረራርቷል። ” ምንም የተለየ ነገር የለም። እግርኳሱን መውደድ፣ ልምምዶችን በአግባቡ መስራት እና ለአንድ ተጫዋች ወሳኝ የሆነው ዲሲፕሊንን አክብሮ መጫወት በጣም አስፈላጊ ነው።” ብሏል። በመጨረሻም ለረጅም ዓመት ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ጌታነህ ከበደ እንዳሻሻለው ሁሉ አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና አዲስ ግደይም ይህን ሪከርድ ማሻሻል አለባችሁ በማለት መልክቱን አስተላልፏል።

ዮርዳኖስ ዓባይ በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ፣ መብራት ኃይል፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ድሬዳዋ ፖሊስ፣ አልሳቅር፣ የኢትዮጵያ ወጣት እና ዋናው ብሄራዊ ቡድን ጣፋጭ 15 ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ባሳለፍነው ዓመት ከጨዋታ ዓለም መግለሉ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡