ወልቂጤ ከተማ ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማማ

አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ወልቂጤ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ለማምጣት በመስማማት የአዳዲስ ተጫዋቾችን ቁጥር አምስት አድርሷል።

ኩዌክ አንዶህ ለወልቂጤ ለመፈረም ከተስማሙት መካከል ነው። ጋናዊው በሀገሩ ክለቦች ኽርትስ ኦፍ ኦክ፣ ኸርትስ ኦፍ ላየንስ እና በረኩም ቼልሲ የተጫወተ ሲሆን ወደ ደደቢት በ2009 አጋማሽ ከመጣ በኋላ በዘንድሮው የውድድር ዓመት አጋማሽ ውሉን አጠናቆ ወደ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ መቐለ 70 እንደርታ አምርቶ ዓመቱን አጠናቋል። የኋላ መስመሩ ላይ ትኩረት እያደረገ በሚገኘው ወልቂጤም በመሐል እና መስመር ተከላካይነት አማራጭ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላኛው አዲስ ተጫዋች ብርሀኑ በቀለ ነው። ተጫዋቹ ደቡብ ፖሊስ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ አስተዋፅኦ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል የነበረ ሲሆን ዘንድሮም በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል። በመስመር በኩል ከተከላካይነት እስከ አጥቂነት መጫወት የሚችልም ነው።

ወልቂጤ ሁለቱንም ተጫዋቾች ለአንድ ዓመት ለማስፈረም እንደተስማማ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡