የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ጨዋታ በዝግ በመካሄዱ ኃላፊነት የሚወስደው ማነው ?

የዛሬው ጨዋታ ከመካሄዱ አስቀድሞ ትናንት አመሻሽ ላይ በኤም ኤ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው ቅድመ ስብሰባ የጨዋታው ኮሚሽነር ዮጋንዳዊው ማይክ ቼን ባ በቅድመ ስብሰባ ላይ ” የድሬዳዋ ስታዲየም የማሻሻያ ስራዎች እየተደረጉበት በመሆኑ አሁን ካለበት ሁኔታ የፀጥታ ችግር ቢፈጠር ሜዳው አጥር የሌለው በመሆኑ ኃላፊነት መውሰድ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ በዝግ መካሄድ አለበት።” በማለት ለካፍ በማሳወቃቸው ከብዙ ክርክሮች በኃላ በሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች በደረሱት ስምምነት ኮሚሽነሩ ፍቃደኛ በመሆን ጨዋታው ለተመልካች ክፍት እንዲሆን ወስነው መለያየታቸውን መዘገባችን ይታወቃል።

ሆኖም ዛሬ ማለዳ ካፍ ለኮሚሽነሩ ጨዋታው በዝግ እንዲካሄድ በኢሜይል ውሳኔ ይደርሳቸዋል። በዚህም መሠረት ኮሚሽነሩ በስታዲየሙ በመገኘት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮች በመሆን ኮሚሽነሩን ለማግባባት ቢሞክሩም ሳይሳካ በመቅረቱ ጨዋታው ያለ ተመልካች በዝግ እንዲካሄድ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ካሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች በመነሳት ጨዋታውን ድሬዳዋ ላይ እንዲካሄድ ማድረጉ መልካም ቢሆንም ጨዋታው ከሚደረግበት ቀናት አስቀድሞ ሜዳው የሚገኝበትን ሁኔታ የመከታተል እና የሚስተካከሉ ጉዳዮችን የማስተካከል ሥራዎችን መስራት ይገባው እንደነበር እሙን ነው። ይህ አለመደረጉን ተከትሎ የጨዋታው ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም ተፅዕኖ ያሳደረባቸው አካላት አሉ


* እግርኳስ አፍቃሪው የድሬዳዋ ህዝብ የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታ የመከታተል ዕድል ከመነፈጉ ባሻገር በተራራ እና ከፍታ ቦታዎች ላይ ተቀምጦ ለማየት ተገዷል።

* ለጨዋታው የመግቢያ ትኬት ህትመት ወጪ ወጥቶ አገልግሎት ላይ ባለመዋሉ ብክነት አስከትሏል።

* ብሔራዊ ቡድኑ የሜዳ ተጠቃሚነቱን ከማጣቱ በተጨማሪ ዋሊያዎቹ በጨዋታው ላይ ከማተኮር ይልቅ ከሜዳ ውጪ የሚኖር የሥነ ልቦና ተፅእኖ ሰለባ ሆነዋል.። ምናልባትም ከጅቡቲ በተሻለ የእግርኳስ ደረጃ ላይ ከሚገኝ ብሔራዊ ቡድን ጋር ቢጫወት ዛሬ ከተገረምንበት ውጤት የባሰው ሊከፋው ሊከሰት ይችል ነበር።

* በካፍ ደንብ መሠረት ያለ ተመልካች በዝግ ይካሄዳል ተብሎ የተወሰነ ጨዋታ መገናኛ ብዙኀን እንዳይገቡም ጭምር ይደነግጋል። በዚህም ምክንያት ጨዋታውን ለህዝብ ለማስተላለፍ የመጡ ሚዲያዎች በሙሉ የመጡበትን ተልዕኮ ሳያሳኩ መጉላላት ደርሶባቸዋል።

ፌዴሬሽኑ ጨዋታው ሊደረግ ሰዓታት ሲቀረው አምስት የስራ አስፈፃሚ አባለት ለፕሮቶኮል ከመላክ ይልቅ የሜዳውን ገፅታ አስቀድመው በመመልከት ሜዳው ያሉበትን ችግሮች ተመልክተው መፍትሄ የሚሰጡ አካላትን መላኩ ተገቢ ነበር።

በአጠቃላይ ዛሬ የተፈጠረው ችግር በቀጣይ በተመሳሳይ እንዳይደገም ኃላፊነት የሚወስደው አካል በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅና አስፈላጊውን የዕርምት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡