ሪፖርት | ኢትዮጵያ በጅቡቲ ተፈትና ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች

የ2020 የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታውን ከጅቡቲ አቻው ጋር በዝግ ስቴዲየም የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደካማ እንቅስቃሴ ተፈትኖ 4-3 በማሸነፍ ወደ መጨረሻው ማጣርያ አልፏል።

የድሬዳዋ ስታዲየም የዕድሳት ማሻሽያ እየተደረገበት በመሆኑ የጨዋታው ኮሚሽነር ሜዳው ለጨዋታ ብቁ አለመሆኑን ለካፍ ያቀረቡት ሪፖርት ተቀባይነት አግኝቶ ጨዋታው በዝግ እንዲካሄድ በመወሰኑ ያለ ተመልካች በዝግ ጨዋታው እንዲካሄድ ሆኗል።

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከመጀመርያው የጅቡቲ ጨዋታ አስቻለው ታመነን በጉዳት ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ፍቃዱ ዓለሙን በማሳረፍ ደስታ ደሙ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሙጂብ ቃሲምን በመቀየር ወደ ሜዳ ገብተዋል። የመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች ጨዋታው ለመገናኛ ብዙሐን ዝግ የነበረ በመሆኑ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ለመግለፅ አስቸጋሪ ቢሆንም ጨዋታውን መከታተል ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ፊት በመሔድም ሆነ አደጋ በመፍጠር ጅቡቲዎች የተሻሉ ነበሩ። በ10ኛው ደቂቃ በጥሩ መንገድ ጅቡቲዎች ሳጥን ውስጥ በመግባት ፉአድ ሮብሌህ ወደ ጎል ሲመታው ግብጠባቂው ምንተስኖት አሎ እንደምንም ሲያድነው የተመለሰውን ኳስ ማሀዲ አግኝቶ ቢመታውም ደስታ ደሙ ተንሸራቶ ጎል ከመሆን ያዳነበት የጅቡቲ ጠንካራ የጎል ሙከራ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይዞት የገባው የጨዋታ አቀራረብ አጥቅቶ ለመጫወት ቢመስልም ሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ግን የተለየ ነበር። በረጃጅም ኳስ ወደ ፊት የሚደርሱት ምንም መቀናጀት ያልቻሉት ዋልያዎቹ በ16ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከመስመር የተጣለለትን ኳስ ወደ ሳጥን ገፍቶ በመግባት ለጓደኞቹ የሚያቀብል መስሎ በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን የጅቡቲው ግብጠባቂ ናስረዲን ይዞበታል። የዕለቱ ሶማሊያዊ ዳኛ በጨዋታው የኃይል አጨዋወት የፈቀዱ በሚመስል መልኩ ጨዋታ ኃይል ወደ ተቀላቀለበት እንቅስቃሴ አምርተቶ የተለያዩ ግልፅ ጥፈቶችን በዝምታ ማለፋቸው የጨዋታውን እንቅስቃሴ ረብሾታል። በዚህ ውጥረት የቀጠለው ጨዋታ 26ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ከተከላካይ ጀርባ ነፃ አቋቋም ላይ የሚገኘው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ተረጋግቶ ደገፍ በማድረግ ለኢትዮጵያ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል።

በዚህች ጎል መቆጠር የተረጋጉ የሚመስሉት ዋልያዎቹ ከደቂቃዎች በኃላ የጅቡቲው ግብጠባቂ ናስረዲን ኳሱን አርቃለው በማለት ያጠረበትን ኳስ አዲስ ግደይ አግኝቶ ብቻውን አምስት ከሃምሳ ውስጥ ለነበረው ለሙጂብ ቃሲም አቀብሎት የጎሉ ቋሚ የመለሰበት የጎል አጋጣሚ የብሔራዊ ቡድኑን ሦነ ልቦና ከፍ ማድረግ የሚችል ነበር። አዲስ ግደይ ከግራ ወደ ቀኝ ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጋር ከተቀያየሩበት 36ኛው ደቂቃ በኃላ ዋልያዎቹ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ለማድረግ እየተጫወቱ ባለበት አጋጣሚ 40ኛው ደቂቃ የጅቡቲ የፊት መስመር ተጫዋቾች ኳሱን አደራጅተው ወደ ፊት በመግባት ተቀይሮ ለገባው የሱፍ ኦማር አቀብለውት የሱፍ በጥሩ አጨራረስ ጎል አስቆጥሮ ጅቡቲዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። የመጀመርያውን ጎል ዋልያዎቹ ባስቆጠሩበት መንገድ በተመሳሳይ 43ኛው ደቂቃ የተገኘውን የማዕዘን ምት በመጠቀም ያሬድ ባዬ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ሁለተኛ ጎል መምራት ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ በ47ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ በተጣለን ኳስ ቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ተከላካዮችን በማለፍ የገባው እና በዛሬው ጨዋታ በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ለሙጂብ ቃሲም አቀብሎት ሙጂብ ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ኳሱን ሲመልሰው አዲስ ግደይ ነፃ ኳስ አግኝቶ የኢትዮጵያን ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ይህች ጎል አዲስ ግደይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተመረጠበት ጊዜ አንስቶ ያስቆጠራት የመጀመርያው ጎሉ ሆና ተመዝግባለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከእረፍት መልስ ወድያውኑ ጎል በማስቆጠሩ በተሻለ መንቀሳቀስ ይችላል ቢባልም ይባስኑ ተዳክሞ ታይቷል። ጎል ቢቆጠርባቸውም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ የቀጠሉት ጅቡቲዎች ከዋልያዎቹ ተከላካዮች ትኩረት ማጣት ተከትሎ 52ኛው ደቂቃ በፉአድ መሐመድ አማካኝነት ሁለተኛውን ጎል አስቆጥረዋል። ኳሱን ይዘው ተረጋግተው ከመጫወት ይልቅ ጫና ውስጥ የገቡት ዋልያዎቹ በተደጋጋሚ በሚሰሩት ጥፋት አራት የማስጠንቀቂያ ካርድ ለመመልከት ተገደዋል። የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍተኛ የነበረው ጅቡቲዎች በአንጻሩ ብዙም ሳይቆዩ በ58ኛው ደቂቃ በማህዲን ማሀቤ አማካኝነት ባስቆጠሩት ሦስተኛ ጎል ሦስት አቻ መሆን ችለዋል። ወድያውኑ ጅቡቲዎች ዋልያዎችን መምራት የሚያስችላቸውን ነፃ የጎል አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ቢሆንም በማይታመን ሁኔታ ማህዲን ሳይጠቀም ቀርቷል።

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ቢያስቡም በቀረው ደቂቃ ምንም የተሻለ ነገር መመልከት አልቻልንም። በመጨረሻም የጅቡቲዎችም ወደ ፊት በመሄድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እየቀዘቀዘ ሲመጣ አንፃሩ ዋልያዎቹ በተቆራረጠ ኳስ እና መድረሻ በሌላቸው ረጃጅም ኳስ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት እየተጫወቱ ባለበት በ88ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ወጣቱ ተስፋኛ አጥቂ መስፍን ታፈሰ አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋን ወደ እርግጠኝኘት ቀይሯል። መስፍን ታፈሰ ያስቆጠራት ጎል በዋናው ብሔራዊ ቡድን በተጫወተበት የመጀመርያ ጨዋታው የመጀመርያው ጎሉ መሆን ችላለች። ጨዋታውም ዋልያዎቹ በጅቡቲ አቻቸው ተፈትን 4-3 በድምሩ 5-3 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡