ባህር ዳር ከተማ ፋሲል ተካልኝን በይፋ አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

በዓመቱ መጨረሻ ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር የተለያዩት የጣናው ሞገዶቹ ዛሬ በይፋ ፋሲል ተካልኝን አሰልጣኝ አድርገው ማስፈረማቸውን አስታውቀዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ፋሲል ተካልኝ ወደ ክለቡ እንደሚመጣ መነገሩ የሚታወስ ሲሆን አሰልጣኙ በብሄራዊ ቡድን ግዳጅ ላይ በመገኘቱ ይፋዊ ስምምነት ሳይደረግ ቆይቷል። አሰልጣኙን ማጣት ያልፈለጉት ባህር ዳሮች ቀደም ብለው ድሬዳዋ ድረስ በማቅናት ቅድመ ስምምነት ማድረጋቸውም ይታወሳል። ዛሬ ጠዋት ደግሞ የክለቡ አመራሮች ከአሰልጣኙ ጋር በአካል በመነጋገር መስማማታቸውን እና አሰልጣኙ ለአንድ ዓመት ክለቡን ለማሰልጠን ፊርማ ማኖሩን ለማወቅ ተችሏል።

አሰልጣኙ በቀጣይ ምክትሎቹን በራሱ መርጦ እንዲያሳውቅ ፍቃድ እንደተሰጠው እንዲሁም ተጨዋቾችን በቶሎ እንዲያዘዋውር እንደተነገረው ተሰምቷል።

በስብስቡ ውስጥ ከሁለት ተጨዋቾች ጋር ብቻ ቀሪ ውል ያላቸው ባህር ዳሮች በቀጣይ አስር የሚደርሱ ተጨዋቾችን ከአሰልጣኙ ጋር በመነጋገር ለመቀነስ እና የሌሎቹን ውል ለማራዘም እንዳሰቡ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡