ባህር ዳር ከተማ የተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾቹን ውል አድሷል

ትላንት እና ከትላንት በስቲያ የስምንት ነባር ተጨዋቾቻቸውን ውል ያደሱት ባህር ዳሮች ተጨማሪ የሁለት ተጨዋቾችን ውል ማደሳቸው ታውቋል።

የጣናው ሞገዶቹ በከፍተኛ ሊግም ሆነ በፕሪምየር ሊግ ባደረጉት ጥሩ እንቅስቀሴ ጉልህ ሚና ሲወጣ የተስተዋለው ወሰኑ ዓሊ ውሉን ለአንድ ዓመት ያደሰ ተጨዋች ነው። ከኢትዮጵያ መድን ወደ ባህር ዳር በማምራት የጨዋታ ህይወቱን የቀጠለው ወሰኑ በተለይ ባሳለፍነው ዓመት ወጥ ብቃቱን በማሳየት ድንቅ ድልጋሎት ሰጥቷል።

ሁለተኛው ውሉን ያደሰ ተጨዋች ግርማ ዲሳሳ ነው። በሁለቱም የፊት መስመሮች (በግራ እና በቀኝ አጥቂነት) መጫወት የሚችለው ግርማ ቡድኑ በጉዳት እና በቅጣት የመስመር ተከላካዮቹን ባጣባቸው ወቅቶች ወደ ኋላ በመመለስ ጥሩ ግልጋሎት አበርክቷል። ወደ ሰበታ ከተማ ሊያመራ ይችላል ተብሎ ሲነገር የነበረው ተጫዋቹ ከጣናው ሞገዶቹ ጋር ለሁለት ዓመት ለመቆየት ተስማምቷል።

ሁለቱን ተጨዋቾች ጨምሮ እስካሁን አስር ነባር ተጨዋቾችን በቡድናቸው ለማቆየት የተስማሙት ባህር ዳሮች በቀጣይ አዲስ ባዋቀሩት የቴክኒክ ክፍል እና ዋና አሰልጣኛቸው (ፋሲል ተካልኝ) የታመነባቸውን አዳዲስ ተጨዋቾች ለማምጣት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ተነግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡