ሰበታ ከተማ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ጀምሯል

ከሰምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሰው ሰበታ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩን ለጊዜው ይፋ ለማድረግ ቢዘገይም በዝውውር መስኮቱ አስራ ስምንት ተጫዋቾችን ለማስፈረም በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር መለያየቱ እርግጥ መሆኑን ተከትሎ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ቀጣዩ አሰልጣኝ አድርጎ ለመሾም ከጫፍ ቢደርስም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሒደቱ ተጨናግፏል። ይህም ሳይሳካ በመቅረቱ ሌላ አሰልጣኝ ለመቅጠር ያልዘገዩት ሰበታዎች ለጊዜው ይፋ ለማድረግ ቢዘገዩም አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ዋና አሰልጣኝ አድርገው መሾማቸውን የሚያሳዩ ምልክቶችን መመልከት ከጀመርን ሰነባብተናል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሰበታ ከነማ በከፍተኛ ሊግ በነበረው ተሳትፎ ከቡድኑ ጋር አብረው ከተጓዙ ተጫዋቾች መካከል ሰባት ተጫዋቾችን ብቻ እንደሚያስቀሩ እና አስራ ስምንት አዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ዕቅዳቸውን ለክለቡ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል። በዚህም መሠረት የዕቅዳቸው አካል የሆኑ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን በትናትናው ዕለት ሁለት ተጫዋቾችን የግላቸው ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በቅርቡ የተለያየው አስቀድሞ በሀዋሳ ከተማ እና በደደቢት የምናቀው ሁለገቡ ተጫዋች በኃይሉ አሰፋ የሰበታዎች ለመሆን ተስማምቷል። ከሀዋሳ፣ ደደቢት እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ከማንሳቱ ባሻገር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስኬታማ ጊዜያት ያሳለፈው በኃይሉ ካለው ከፍተኛ ልምድ በመነሳት አዲስ አዳጊዎቹን በበቂ ሁኔታ ያገለግላል ተብሎ የሚጠበቅ ተጫዋች ሆኗል።

ሌላኛው ለክለቡ ለመጫወት የተስማማው ከስልጤ ወራቤ አንስቶ በወላይታ ድቻና መከላከያ ጥሩ የውድድር ጊዜ ያሳለፈው የኋላ ደጀኑ አዲስ ተስፋዬ ነው። የኢትዮጵያ ዋንጫን ከመከላከያ ጋር ሁለት ጊዜ በማንሳት የቻለው አዲስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለ ሲሆን የሰበታን የኃላ መስመር ያጠናክራል ተብሎ የሚጠበቅ ተጫዋች ሆኗል።

በቀጣዮቹ ቀናት በተለይም ሰኞ ሰበታ ከተማን የሚቀላቀሉ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡