በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ነገ አዛምን ይገጥማል

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ የኢትዮጵያው ፋሲል ከነማ ዳሬ ሰላም ላይ ከታንዛኒያው አዛም ጋር ነገ ጨዋታውን ያደርጋል።

19 ተጫዋቾችን በመያዝ ከትላንት በስቲያ ወደ ዳሬ ሰላም ያመሩት ፋሲል ከነማዎች በሀገሪቱ ብሔራዊ ስታዲየም የልምምድ ሜዳ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ የነገውን ጨተታ በሚያደርጉበት ስታዲየም ልምምድ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ረፋድ ላይ በቀደሙት ቀናት ባከናወኑበት ሜዳ ልምምዳቸውን አድርገው ለነገው ጨዋታ የሚያደርጉትን ዝግጅት አገባደዋል። ሁሉም ተጫዋቾች በተሟላ ጤንነት እና በጥሩ የጨዋታ መንፈስ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።

በመጀመርያው ጨዋታ ከ15 ቀናት በፊት ባህር ዳር ላይ በበዛብህ መለዮ ብቸኛ ጎል 1-0 ያሸነፉት ፋሲል ከነማዎች በአዲሱ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እየተመሩ ውጤት አስጠብቀው ወደ ቀጣይ በማለፍ የመጀመርያ የአፍሪካ ተሳትፏቸውን በውጤት ለማጀብ አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ። አሰልጣኙ ወደ ዳሬ ሰላም ከማምራታቸው ቀደም ብሎ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየትም ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳዮች ጥንቃቄ በማድረግ የባህር ዳሩን ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

በአዲሱ ክለባቸው ነገ የመጀመርያ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ከዚህ ቀደም የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ልምድ ያላቸው ሲሆን ዓምና ከመከላከያ ጋር በውድድሩ ላይ ቀርበው በናይጄርያው ሬንጀርስ ኢንተርናሽናል በድምር ውጤት ተሸንፈው መሰናበታቸው የሚታወስ ነው።

ነገ 10፡00 ላይ በአዛም ኮምፕሌክስ የሚደረገውን ጨዋታ በድምር ውጤት አሸንፎ የሚያልፈው ቡድን በቀጣይ የማጣርያ ዙር (ወደ ምድብ ለመግባት) የብሩንዲው ቱኪንዞ እና የዛምቢያው ትሪያንግልስ አሸናፊን የሚገጥም ይሆናል።

ፎቶ – ከፋሲል ከነማ የፌስቡክ ገፅ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡