ሴካፋ ከ20 ዓመት በታች | ኢትዮጵያ ከምድብ ለመሰናበት ተቃርባለች

የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ አራተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሽንፈቷን አስተናግዳለች። ኬንያ እና ታንዛንያም ነጥብ ተጋተርዋል።

አስቀድሞ የተከናወነው የኢትዮጵያ እና ዛንዚባር ጨዋታ በዛንዚባር 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ኢትዮጵያ ከመጀመርያው ጨዋታ ለውጦችን በማድረግ በተለይም በቻን ማጣርያ ሩዋንዳን በገጠመው ስብስብ የመጀመርያ ተሰላፊ የነበረው መስፍን ታፈሰን ብትጠቀምም በደካማዋ የእግርኳስ ሀገር ሽንፈት አስተናግዳለች።

ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ዛንዚባሮች በ17ኛው ደቂቃ በሳዳም ማካሜ አማካኝነት ሲሆን በ51ኛው ደቂቃ አበባየሁ አጪሶ ኢትዮጵያን አቻ አድርጓል። ጨዋታው በዚህ ውጤት ሊጠናቀቅ ተጨማሪ ደቂቃዎች ሲቀሩ ካሌድ ሻባን መብሩክ የዛንዚባርን የድል ጎል አስቆጥሮ የሀገሪቱን የማለፍ ተስፋ ሲያለመልም ኢትዮጵያም ተከታታይ ሽንፈቷን አስተናግዳለች።

ቀጥሎ የተከናወነው የኬንያ እና ታንዛኒያ ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ኬንያ በአቲዬኖ ኦዲዬምቦ እና ፓትሪክ ኦቲዬኖ ጎሎች ሁለት ጊዜ የመምራት እድል ብታገኝም ታንዛኒያዎች በአንድሪው አልበርት እና አብዱልሀሚስ ሱሌይማን ጎሎች ሁለት ጊዜ አንሰራርታ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

የዚህ ምድብ ቀጣይ እኛና የመጨረሻ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ሲደረጉ በ8 ሰዓት ኢትዮጵያ ከኬንያ፤ በ10:00 ደግሞ ዛንዚባር ከታንዛኒያ ይጫወታሉ።

የምድብ ለ የደረጃ ሰንጠረዥ

ቡድን ተጫ (ልዩ) ነጥብ
1 ኬንያ 2 (+5) 4
2 ታንዛኒያ 2 (+4) 4
3 ዛንዚባር 2 (-4) 3
4 ኢትዮጵያ 2 (-5) 0

የነገ ጨዋታዎች
8:00 ኤርትራ ከ ጅቡቲ (ምድብ 1)
10:00 ዩጋንዳ ከ ሱዳን (ምድብ 1)
10:00 ደቡብ ሱዳን ከ ሶማሊያ (ምድብ 3)


© ሶከር ኢትዮጵያ