ትግራይ ዋንጫ| አክሱም ከተማ የምድቡን መሪ የሆነበትን ድል አስመዝግቧል

የትግራይ ዋንጫ ዛሬ ሲጀምር በደደቢት እና አክሱም ከተማ መካከል የተካሄደው የመክፈቻ ጨዋታ በአክሱም ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በተመጣጣኝ ፉክክር የጀመረው ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል በርካታ ሙከራዎች የታየበት ሲሆን ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በኃላም የአክሱም ከተማ ፍፁም ብልጫ የታየበት ነበር። ዳዊት ዑቅበዝጊ ከመስመር አሻምቷት ፉሴይኒ ኑሁ በግንባሩ ባደረጋት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ሰማያዊዎቹ ምንም እንኳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አንቶኒዮ አቡዋላ ከቅጣት ምት ያደረጋት ለግብ የቀረበች ሙከራ እና ፉሴይኒ ኑሁ ከርቀት አክርሮ መትቶ አሸብር ደምሴ ያዳናት ሙከራም ይጠቀሳሉ።

በአጋማሹ ብልጫ የነበራቸው አክሱም ከተማዎችም በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም ዘካርያስ ፍቅሬ በተከላካዮች ስህተት አግኝቶ ያመከናት ዕድል እና ግዮን መልአክ ከመአዝን የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። በሃያ ሶስተኛው ደቂቃም የአማካዩ አዲስዓለም ደሳለኝ ከርቀት ባስቆጠራት ግሩም ግብ አክሱም ከተማዎች መሪ መሆን ችለዋል።

አክሱም ከተማዎች ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ብዙም ሳይቆዩ በዘካርያስ ፍቅሬ አማካኝነት ጥሩ የግብ አጋጣሚ ቢያገኙም አጥቂው ብቻው ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ዕድሉ አምክኖታል። በሰላሳ ስምንተኛው ደቂቃም ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት የተገኘችው ቅጣት ምት ዘካርያስ ፍቅሬ አስቆጥሮ አክሱም ከተማዎች ሁለት ለባዶ እንዲመሩ አስችሏል። በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ደቂቃዎችም ቃልኪዳን ዘልአለም ግብ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ማጥበብ ችሏል።

ከመጀመርያው አጋማሽ በብዙ መልክ የተለየ እንቅስቄሴ እና የደደቢት ብልጫ የታየበት ሁለተኛው በርካታ የግብ ሙከራዎች ያልታየበት ነበር። ክፍሎም ሐጎስ ከቅጣት ምት ባደረገው ሙከራ ወደ ተጋጣሚ ግብ መድረስ የጀመሩት ሰማያዊዎቹ ከዳንኤል አድሐኖም በሚነሱ ረጃጅም ኳሶ የተሻሉ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ዳንኤል አድሐኖም አሻምቶ ከግቡ ቅርብ ርቀት የነበረው ቃልኪዳን ዘልአለም ያመከነው እጅግ አስቆጪ የግብ ዕድል ይጠቀሳል። ፉሴይኒ ኑሁ ከርቀት ያደረገው ሙከራም ሌላ የሚጠቀስ ሙከራ ነው።

በሰማንያኛ ደቂቃ ዘካርያስ ፍቅሬ ከመስመር የተሻማችው ኳስ በግሩም ሁኔታ በግንባር በማስቆጠር የቡድኑ መሪነት አጠናክሯል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ መድሃኔ ታደሰ ከቢንያም ደበሳይ በግንባር የተላከችለት ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ውጤቱን ማጥበብ ችሏል። በተጨማሪ ደቂቃም በአንቶንዮ አብዋላ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘው ፍፁም ቅጣት ምት ቢንያም ደበሳይ መትቶ ወደ ግብነት ሳይቀይራት ቀርቷል።

ውጤቱ በዚ መጠናቀቁ ተከትሎ አክሱም ከተማዎች ምድባቸው መምራት ጀምረዋል። በጨዋታው ሁለት ግቦች ያስቆጠረው የአክሱም ከተማው አጥቂ ዘካርያስ ፍቅሬም ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ