ከ1 ወር መቋረጥ በኋላ ትላንት በተደረጉ ጨዋታዎች ከቆመበት የቀጠለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ሲረከብ ኢትዮጵያ ቡና ደረጃውን ያሳሳለበት ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ደደቢትም በሜዳው አቻ ተለያይቷል፡፡
በ9፡00 አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ደደቢት 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡ ደደቢት በግብ አዳኙ ሳሙኤል ሳኑሚ የ21ኛ ደቂቃ ግብ መምራት ቢችልም ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ከጉዳት የተመለሰው ተሸመ ታደሰ እንገዳዎቹን አቻ አድርጓል፡፡ ቀሪው ረጅም የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ግብ ሳቆጠርበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ደደቢት አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አርባምንጭ ከተማ 2 ደረጃዎች አሻሽሎ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በ10፡00 አበበ ቢቂላ ላይ ዳሽን ቢራን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና 2-0 በማሸነፍ ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግሟል፡፡ ደረጃውንም አሻሽሏል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ የድል ግብ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየው ኤልያስ ማሞ በ28ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር ካሜሩናዊው ያቤውን ዊልያም በ83ኛው ደቂቃ ከኤልያስ ማሞ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች የዳሽን ቢራው ተከላካይ ያሬድ ባየህ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ምክንያት በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ደረጃውን ወደ 5ኛ ከፍ ሲያደርግ ዳሽን ቢራ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ11፡30 በተደረገው የእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን 3-0 አሸንፎ የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ከአዳማ ከተማ ተረክቧል፡፡ አንጋፋው አዳነ ግርማ በ49ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይሮ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ሲያደርግ በ66ኛው ደቂቃ በድጋሚ አዳነ ግርማ ሁለት የድቻ ተከላካዮችን አልፎ በግራ እግሩ በግሩም ሁኔታ 2ኛውን አክሎ የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ አዳነ ያስቆጠረውን የግብ መጠን ወደ 6 በማሳደግ ከሳሙኤል ሳኑሚ እና ታፈሰ ተስፋዬ ጋር የከፍተኛ ግብ አግቢውን ሰንጠረዥ መጋራት ችሏል፡፡ በ83ኛው ደቂቃ ደግሞ ዩጋንዳዊው ኢንተርናሽናል ብሪን ኡሞኒ ሶተኛውን አክሎ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው ወንድማገኝ በለጠ በሁለት ቢጫ ከሜዳ መወገዱን ተከትሎ ድቻዎች የሁለተኛውን አጋማሽ አመዛኝ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ10 ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል፡፡ ድሉን ተከትሎ ፈረሰኞቹ በ19 ነጥብ ነገ ጨዋታውን ከሚያደርገው አዳማ ከተማ ጋር በነጥብ ተስተካክሎ በግብ ልዩነት በመብለጥ የሊጉን መሪነት ሲጨብጡ 4ኛ ተከታታይ ሽንፈት ስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች በ9 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ሊጉ ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች የ8ኛ ሳምንት መርሃ ግብሩን ሲያገባድድ አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል፡፡ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ደግሞ በ11፡30 መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማል፡፡
የደረጃ ሰንጠረዡ ይህንን ይመስላል፡-
የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-