የሴካፋ ዋንጫ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይጀምራል

የሴካፋ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን እና ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከሁለት ሳምንት በኋላ መካሄድ ይጀምራል።

በተለያዩ ጊዜያት ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች በመጥፋታቸው ምክንያት እየተቆራረጠ ለመደረግ የተገደደው የሴካፋ የወንዶች ሻምፒዮና ውድድር ከዘንድሮ ከኅዳር 27 – ታኅሳስ 9 በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እንደሚደረግ በታንዛኒያ እየተደረገ ባለው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ላይ ለጋዜጠኞች በተሰጠ መግለጫ ተጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ ለመጀመርያ ጊዜ የሚከናወነው የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በተመሳሳይ ቀን ይጀመራል የተባለ ሲሆን እስከ ታኅሳስ 9 እንደሚቆይ ተገልጿል።

እስካሁን በውድድሩ ላይ እንደማትሳተፍ ካሳወቀችው ሩዋንዳ ውጪ ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እንደሚሳተፉ የገለፀ ሲሆን የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሊቢያ በተጋባዥነት በውድድሩ ላይ ብቅ እንደምትል ታውቋል፡፡

ሴካፋ ውድድሩን አስመልክቶ ለሀገራት እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ከ15 ቀናት አስቀድሞ በላከው ደብዳቤ መሠረት ሀገራት ቡድኖቻቸውን እያዘጋጁ ሲሆን እንደ ቡሩንዲ ያሉ ሀገራትም ከወዲሁ የቡድን ስብስባቸውን እያሳወቁ ይገኛሉ። አንደኛዋ የውድድሩ ተሳታፊ ሀገር ኢትዮጵያም ለውድድሮቹ ስለምታደርገው ዝግጅት አዳዲስ ነገሮች በቀጣይ ቀናት ይታወቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ