ሰበታ ከተማ እና አሞሌ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

የዘመናዊ የስታዲየም መግቢያ ትኬት ሽያጭን ይዞ ብቅ ያለው አሞሌ ከሰበታ ከተማ ጋር ዛሬ መፈራረሙን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ምንዳ ለሶከር ኢትዮጵያ ገለፁ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በስታዲየም በሮች ላይ ሲደረግ የነበረውን የእጅ በእጅ የትኬት ሽያጭን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በዘመናዊ የትኬት አሰራር ተመልካቾች በዳሽን ባንክ አሞሌ ሲስተም በኩል ትኬት ቆርጠው ወደ ስታዲየም እንዲገቡ ሲደረግ እንደነበር ይታወሳል።

ይህን የተቀላጠፈ ዘመናዊ አሰራር ከአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመቀጠል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ተግባራዊ ለማድረግ ከአሞሌ ጋር ስምምነት የፈፀሙ ሲሆን ሰበታ ከተማ ደግሞ ከሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች በመቀጠል ሦስተኛ ክለብ ሆኗል፡፡

የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ምንዳ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ሰበታ ከተማ በሦስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ አበባ ስታዲየም አዳማ ከተማን ሲገጥም ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በተመረጡ በሁሉም የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች በመገኘት ተመልካቹ የመግቢያ ትኬቶቹን ማግኘት እንደሚችል ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ለአንድ አመት ያህል ከድርጅቱ ጋር ስምምነት የፈፀመው ክለቡ የሰበታ ስታዲየም ከተጠናቀቀ በኃላም ይህ አሰራር ተፈፃሚ ይደረጋል ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ