ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ነገ ከሚደረጉ የ4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን የሚገጥምበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በ3ኛ ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት የጣና ሞገዶቹ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እንዲሁም ብርትካናማዎቹ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ ያገኙትን የባለፈው ሳምንት ሦስት ነጥብ ዳግም ለማግኘት የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ባህር ዳሮች ኳስን በመቆጣጠ ላይ አተኩረው የሊጉን ጨዋታዎች እያከናወኑ ይገኛሉ። በአንፃራዊነት ጥራት ያላቸው የአማካይ መስመር ተጨዋቾችን የያዘው ቡድኑ ተጋጣሚን የሚያደክሙ የኳስ ቅብብሎችን ሲፈፅም ይታያል። ይህ ደግሞ በተለይ የዐምና የፕሪምየር ሊጉን አሸናፊ በሜዳው ጋብዞ በረታበት ጨዋታ ተስተውሏል። ነገም ቡድኑ በሜዳው እንደመጫወቱ ከተጋጣሚው ድሬዳዋ በተሻለ ከኳስ ጋር ያሉ ንክኪዎችን በማብዛት ጨዋታውን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ውጪ ባህር ዳሮች በመስመር ላይ አጨዋወታቸው እና በቆሙ ኳሶች አጠቃቀማቸው ነገ ለድሬዳዋዎች ፈታኝ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በተለይ ቡድኑ በአካላዊ ቁመናቸው ዘለግ ያሉ ተጨዋቾችን (ማማዱ ሲዲቤ፣ አዳማ ሲሶኮ እና አቤል ውዱን) በመያዙ ድሬዳዋዎች በቆመ ኳስ ለማጥቃትም ሆነ ለመከላከል ሊቸገሩ እንደሚችል ይገመታል።

በባለሜዳዎቹ በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለም። በሁለተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ቡድኑ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም መቐለ 70 እንድርታን ገጥሞ 3-2 በረታበት ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ዜናው ፈረደ ከመጠነኛ ጉዳቱ በማገገሙ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ተነግሯል።

በተጋባዦቹ በኩል መነቃቃቶች ያሉ ይመስላሉ። በተለይ ቡድኑ የመጀመሪያ የዓመቱን 3 ነጥብ በሜዳው ማግኘቱን እና ዋና አሰልጣኙ ስምዖን ዓባይ ከቅጣት በመመለሱ ምክንያት በቡድኑ አካባቢ የሚነፍሱ አየሮች ተለውጠዋል። ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት የሊጉን አዲስ ክለብ ሃዲያ ሆሳህናን ገጥሞ በረታበት ጨዋታ ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው ጨዋታዎች የተሻሻለ እንቅስቃሴ ያሳየበት ሆኖ አልፏል።

ድሬዳዋዎች ከሜዳቸው ውጪ ባደረጓቸው ጨዋታዎች የመሃል ሜዳውን በበላይነት ለመቆጣጠር እና ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን ለማሰልጠን 5 የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ምርጫቸው እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት አሰልጣኝ ስምዖን ከባለሜዳዎቹ የሚሰነዘሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ከምንጩ ለመመከት እና ጨዋታውን በእጃቸው ለማድረግ ጥረቶችን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ውጪ በነገው ጨዋታ ቡድኑ ሪችሞንድ ኦዶንጎን ኢላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም የባህር ዳር ከተማ ተጨዋቾች ትተዋቸው የሚወጡትን ሜዳዎችን በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም እንደሚጥሩ ይገመታል።

በድሬ በኩል ተከላካዩ ያሬድ ሀሰን እና አማካዩ ረመዳን የሱፍ አሁንም በጉዳት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ከቡድኑ ጋር ያልተጓዙ ሲሆን ከሰሞኑ ቀዶ ጥገና እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ምንያህል ተሾመም ግልጋሎት አይሰጥም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ዐምና ሲሆን ባህርዳር በሜዳው፣ ድሬዳዋም በሜዳው በተመሳሳይ 2-1 አሸንፈዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪሰን ሄሱ

ሳላምላክ ተገኝ – አዳማ ሲሶኮ – አቤል ውዱ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ሳምሶን ጥላሁን – ፍ/ሚካኤል ዓለሙ – ፍፁም ዓለሙ

ግርማ ዲሳሳ – ወሰኑ ዓሊ – ማማዱ ሲዲቤ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1/4-5-1)

ፍሬው ጌታሁን

ያሬድ ዘውድነህ- በረከት ሳሙኤል (አ)- ዘሪሁን አንሼቦ- አማረ በቀለ

አማኑኤል ተሾመ- ዋለልኝ ገብሬ

ያሬድ ታደሰ – ኤልያስ ማሞ – ሳሙኤል ዘሪሁን

ሪችሞንድ ኦዶንጎ


© ሶከር ኢትዮጵያ