የድሬዳዋ ከተማ ደካማ አጀማመር እና የተጫዋቾች ጉዳት

በቴዎድሮስ ታከለ እና ዓለማየሁ አበበ

በሊጉ ጥሩ ያልሆነ ጅማሬ ካደረጉ ክለቦች መካከል የሆነው ድሬዳዋ ከተማ ነገ ሁለተኛ የሜዳው ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደርጋል። ጉዳት ላይ የሰነበቱት የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ወቅታዊ ሁኔታ እና በክለቡ ደካማ አጀማመር ዙርያ የአሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ አስተያየትን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

ቡድኑ ከዓምና ስብስቡ በርካታ ለውጥ አድርጎ ከመጀመሩ ባለፈ የተዳከመ የተከላካይ መስመር መያዙ ለደካማ አጀማመሩ ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ሲሆን የተጫዋቾች ጉዳትም በተሟላ ስብስብ ጨዋታዎችን እንዳያደርግ እያገደው ይገኛል። አምበሉ ሳምሶን አሰፋ፣ ሁለተኛው አምበል ረመዳን ናስር እና አማካዩ ምንያህል ተሾመን እስካሁን መጠቀም ያልቻው ክለቡ የያሬድ ሀሰን እና ያሬድ ታደሰን ግልጋሎትንም በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ በክረምቱ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት እንዳጋጠመው የሚታወስ ሲሆን ከጉዳቱ ሳያገግም ወደ ልምምድ ቶሎ በመመለሱ ምክንያት ጉዳቱ ዳግም አገርሽቶበት ያለፉትን ሁለት ወራት ከሜዳ ርቆ መቆየቱን ገልጿል። ሳምሶን አሁን ላይ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ከባለፈው ሳምንት አንስቶ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በጋራ በመሆን ልምምድ የጀመረ ሲሆን ክለቡ በቀጣይ በሚያደርጋቸው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ለመጫወት ዝግጁ እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

በክለቡ 10 ዓመታትን የቆየውና ባለፈው የውድድር ዓመት ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው ረመዳን ናስር ላለፉት 45 ቀናት ከሜዳ ርቋል። ቡድኑ በቢሾፍቱ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት የባት ጉዳት ያስተናገደው ረመዳን ከ15 ቀናት በኋላ ከሚኖረው የህክምና ቀጠሮ በኋላ ወደ ሜዳ ሊመለስ እንደሚችል ተናግሯል። “ቡድኔን በምችለው አቅም ባለመርዳቴ አዝናለው፤ ከ 15 ቀን በኋላም በሚኖረኝ ህክምና መሰረት ወደ ሜዳ በመመለስ ቡድኔን ለማገዝ አስባለው።” ሲልም ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

አማካዩ ምንያህል ተሾመ ሌላው በጉዳት ከሜዳ የራቀ ተጫዋች ነው። ባለፈው ዓመት አጋማሽ ቡድኑን የተቀላቀለው ምንያህል በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ከ3 ወራት በላይ ከሜዳ ለመራቅ ተገዷል። “በካዲስኮ ሆስፒታል በጀርመናዊ ዶክተር አማካኝነት ሰርጀሪ አድርጌያለሁ። ዶክተሩ በተለያየ ጊዜ ስለሚመጣ እሱን ጠብቄ ላደርግ ችያለሁ። ወደ እግርኳሱ መቼ እንደምመለስ አላውቅም። ገና ነገ ነው  የማውቀው፤ የታሰረልኝ ሲፈታ እንደሚነግረኝ ነግረውኛል። ህመም ላይ እያለውም መሮጥ እና መንቀሳቀስ እችላለሁ። ሆኖም ኳስ ስጫወት ስለሚያመኝ እና ጥንቃቄ ማድረግ አለብኝ ብዬ ነው ይህን የወሰንኩት” ሲል ስላለበት ሁኔታም ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ጥር 30 ውሉ የሚጠናቀቀው ምንያህል ተሾመ አንደኛውን ዙር ጨምሮ እስከ ሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ሳምንት ድረስም ከሜዳ ይርቃል።

የድሬዳዋ ደካማ አጀማመር በአሰልጣኝ ስምዖን እይታ

ቡድኑ ከአራት ጨዋታዎች መካከል ሦስቱን ከሜዳው ውጪ አድርጎ በሁሉም የተሸነፈ ሲሆን በሜዳው ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ባስመዘገበው ድል ታግዞ በሦስት ነጥቦች ከወገብ በታች ይገኛል። ቡድኑን በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ያልመሩት አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ቡድኑ ደካማ አጀማመር ያደረገበትን ምክንያት በዚህ መልኩ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

” የድሬዳዋ የዚህ ዓመት አጀማመሩ መልካም የሚባል አይደለም። ቡድኑን ከተረከብኩበት ጊዜ አንስቶም ባለፍት አራት ሳምንታት ቡድኑን ያጋጠመው አይነት ውጤት ከዚህ በፊት አላጋጠመውም። የተመዘገቡብን ውጤቶችም ቡድኑን በፍፁም አይገልፀውም። ቡድኑ ባለፍት ሁለት ዓመታት የሚታወቅበትና በተለይም የድሬዳዋ ከነማ ጠንካራ ጎኑ የምለው የተከላካይ መስመሩ ነው በያዝነው ዓመት ግን ይሄ ጠንካራ ጎን በቡድኑ ውስጥ እንብዛም አይታይም። ይህ የሆነበት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም በዋናነት ግን ከዚህ ቀደም በክለቡ ውስጥ የነበሩት ጠንካራ ተጫዋቾች አለመኖራቸውና በምትኩ ያመጣናቸው ወጣቶችና አዳዲስ ተጫዋቾች ከነባሮቹ ጋር ለማዋሀድ ጊዜ መውሰዱ የሚጠቀስ ነው።

” ከዚህ ባለፈ ከሜዳ ውጪ ባደረግናቸው ጨዋታዎች በተለይም ጎንደር ላይ ከፋሲል ጋር በነበረን ጨዋታ በሰፊ ጎሎች በመሸነፋችን ምክንያት በአጠቃላይ ቡድኑ ላይ ጫና ውስጥ እንዲገቡ ሆኗል። የቡድኑ ተጫዋቾቹም ከገቡበት ጫና እንዲወጡ በስነ-ልቦና ባለሞያ በመታገዝ የተለያዩ ትምህርቶች እየሰጠን እንገኛለን። በታክቲክ ረገድ የተወሰኑ ለውጦችን እያደረግን ቢሆንም ትልቁ ነገር ግን ለቀጣይ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት የተጫዋቾች ስነ-ልቦና ላይ መስራት ስለሚገባን ይህንን በመስራት ላይ እንገኛለን።

” ድሬዳዋ ከነማ አሁን ላይ ካለበት ደረጃ ለመውጣት ከፍተኛ ስራ መስራት ይጠበቅብናል። እነዚህንም ስራዎች ለመስራት ደግሞ ብዙ አጋዥ ነገሮች ያስፈልጋሉ። በተለይ ሜዳችን ላይ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች የደጋፊዎቻችንን ድጋፍ በእጅጉ እንፈልጋለን። ከሜዳችን ውጪ ብንሸነፍም በሜዳችን ላይ ግን በተቻለን መጠን ከደጋፊዎቻችን ጋር በጋራ በመሆን ውጤት ለማምጣትና ለማሸነፍ እንሞክራለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ