የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 ሀዋሳ ከተማ

አንድ ለአንድ ከተጠናቀቀው የአዳማ ከተማ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል።


👉 “በርከት ያሉ እድሎችን ብንፈጥርም ወደ ግብነት መቀየር አልቻልንም” ደጉ ዱባሞ (አዳማ ከተማ – ምክትል አሰልጣኝ)

ስለ ጨዋታው እና ስለ ቡድኑ ግብ የማስቆጠር ችግር

በጨዋታው ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ለማጥቃት ሞክረናል። እንደ ከዚህ ቀደሙ ግብ አካባቢ የነበሩ ችግሮች ዛሬም ታይተዋል። በርከት ያሉ እድሎችን ብንፈጥርም ወደ ግብነት መቀየር አልቻልንም። እግር ኳስ ሂደር ይፈልጋል። በአንዴ የሚስተካከል ነገር ላይኖር ይችላል። በቀጣይ የአጨራረስ ብቃታችንን ለማሳደግ ስራዎችን እንሰራለን።

እኛ በሜዳችን ብንጫወትም የሜዳ ላይ ጥቅሞችን እያገኘን አይደለም። በጨዋታው ዳኛውም ተፅዕኖ አድርጎብናል። ዳኛው ለእኛ በሶስተኛው አጋጣሚ ነው የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠን። ለእነሱ ግን ገና በአንደኛው ነው የፍፁም ቅጣት ምት የሰጣቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ስለተከተሉት የጨዋታ ዕቅድ

በሁለተኛው አጋማሽ እኛ ጨዋታውን ለመቆጣጠር አስበን ነበር። ለዚህም ደግሞ የተከላካይ ቁጥር ቀንሰን ኳስ ለመያዝ የሚያስችሉ ተጨዋቾችን አስገብተን ነበር። ግን እንዳሰብነው እና እንደጠበቅነው አልሆነልንም።

👉 “በጨዋታው ያገኘነው አንድ ነጥብ በጣም ይገባናል” አዲሴ ካሣ (ሀዋሳ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ከባድ ነበር። በሁለታችንም በኩል የነበረው የማሸነፍ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነበር። ከምንም በላይ ግን ተጨዋቾቼን ማመስገን እፈልጋለሁ። በጣም ታግለው ነው የተጫወቱት። አዳማዎች ከእኛ የተሻለ ለማጥቃት ሲሞክሩ ነበር። ነገር ግን ተጨዋቾቼ የሚገባውን አድርገው ከጨዋታው ነጥብ ይዘን ወጥተናል። ከሜዳ ውጪ ሁል ግዜ ነጥብ ይዘህ ለመመለስ ነው መጣር ያለብህ።

በመጀመሪያው አጋማሽ ስለተከተሉት አጨዋወት

እንደገለፅኩት ሁል ጊዜ ከሜዳ ውጪ ነጥብ ይዘህ ለመመለስ ነው መታተር ያለብህ። ለዚህም ነው ወደራሳችን የግብ ክልል ተጠግተን ጨዋታውን ያከናወነው። የመጀመሪያ እቅዳችን በመልሶ ማጥቃት ግብ ማስቆጠር የሚል ነበር። ግን እነሱ በጣም ጠጣር ስለነበሩ ይህንን ማድረግ አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ማድረግ የሚገባንን ተግብረን ነጥብ ይዘን ወጥተናል። ግብ ካስቆጠርንባቸው በኋላ ነቅለው ነበር ሲያጠቁ የነበረው። ይህንን ነገር በመልሶ ማጥቃት መጠቀም እንችል ነበር። ነገር ግን ይህንን አልተጠቀምንም።

ስለተገኘው አንድ ነጥብ ተገቢነት

ከጨዋታው አንድ ነጥብ በጣም ይገባናል። ምክንያቱም ማድረግ የሚገባንን አድርገን ስለወጣን አንድ ነጥቡ ይገባናል። እንደውም ከነበረባቸው ክፍተት አንፃር ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር እንችል ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ